ኢትዮጵያ ያላትን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ለአለም በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የበለጠ መስራት ይገባል - የዩኔስኮ ዳይሬክተር

189

አዲስ አበባ መስከረመ 17/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያላትን አስገራሚ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ለአለም በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የበለጠ መስራት እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ዳይሬክተር ዩኒኮ ዩኮዚኪ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በአለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች ውሰጥ የመስቀል በዓል አንዱ ነው።

በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የታደሙት በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ዳይሬክተር ዩኒኮ ዩኮዚኪ ለኢዜአ እንደተናገሩት የዓለም ቅርስ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ መቀጠሉን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ2013 በማይዳሰሱ የአለም ቅርስነት መመዝገቡን አውስተው በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ጨምረው ጠቅሰዋል።

በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የሚቀርቡ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርአቶች፣ የህዝቡ አንድነት፣ መተባበርና የአለባበስ ስርአት የበዓሉን ይዘት ጠብቀው መቀጠሉን ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው ይዘቱን ጠብቆ ማስቀጠል ተገቢ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የመስቀል በዓልን ጨምሮ ያላትን አስደናቂ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት አለም እንዲያውቅ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዩኔስኮ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን ለአለም ለማስተዋወቅ በአቅም ግንባታና ሌሎች የትብበር መስኮች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በቀጣይም በቱሪዝምና ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ላይ የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የተለያዩ የአለም አገራት ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የመስቀል በዓልን አስገራሚና ደማቅ ትዕይንቶች እንዲካፈሉ ዳይሬክተሯ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች አስገራሚ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ያላት አገር በመሆኗ የማስተዋወቅና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራ መጠናከር እንዳለበተም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም