ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል እንድትወጣ ለመከላከያ ሰራዊት የሚደረገውን ሁለንተናዊ የደጀንነት ሚና አጠናክረን እንቀጥላለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

89

መስከረም 17/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል እንድትወጣ ለመከላከያ ሰራዊት የሚደረገውን ሁለንተናዊ የደጀንነት ሚና አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ-ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በጦር ኅይሎች ሆስፒታል በመገኘት ለአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ማዕድ አጋርቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ለህዝብ ሰላም እና የአገር ሉዓላዊነት ከሚዋደቅ ሰራዊት ጋር በዓልን ማሳለፍ ከክብር በላይ ክብር ነው።

የማዕድ ማጋራቱ መከላከያ ሰራዊቱ ከሚከፍለው ዋጋ ጋር የሚስተካከል ሆኖ ሳይሆን ለሰራዊቱ ያለንን አክብሮትና ደጀንነት ለማረጋገጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከገጠሟት ፈተናዎች በድል እንድትወጣ ከተማ አስተዳድሩ ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ የደጀንነት ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ-ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጀማሉ ጀንበር በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት ከውጭ ግብረ አበሮቹ ጋር በማበር የከፈተው ጦርነት በጀግናው መከላከያ ሰራዊት እየተመከተ ይገኛል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት አጋርነቱን ለማሳየት ከበጎ ፈቃደኛ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ በማሰባሰብ በመስቀል በዓል ማዕድ በማጋራቱ ክብር ይሰማዋል፤ ድጋፉንም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የጦር ኃይሎች አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ዶክተር ኅይሉ እንዳሻው በበኩላቸው ሀዝብና መንግስት ለመከላከያ ሰራዊት እያደረጉ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ለሰራዊቱ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዕለቱ ለተደረገው የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብርም አመስግነዋል።

ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት በግንባር ከሚፈጽመው ጀብድ ባሻገር የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና ሰብል በማጨድ ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የወያኔ ሴራ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱ እስኪፈፀም ድረስ የሚደረገው የደጀንነት ሚና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም