መስቀል ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር፣ የአገራችን ስም በበጎ በማስጠራት፣ ባህላችን በማስተዋወቅና አንድነትን በማጠናከር የበዛ ትሩፋት አለው_አምባሳደር ስለሺ በቀለ

111

መስከረም 17 ቀን 2015(ኢዜአ) መስቀል ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር፣ የአገራችን ስም በበጎ በማስጠራት፣ ባህላችን በማስተዋወቅና አንድነትን በማጠናከር ረገድ የበዛ ትሩፋት አለው ሲሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመስቀል ደመራ በዓልን በደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በድምቀት አክብረዋል።

በደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን በተደረገው ክብረ በዓል ላይ አምባሳደር ስለሺ በቀለ፣ የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች እና አባቶች ታድመዋል።

May be an image of 1 person, standing and indoor

ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል ባስተላለፉት መልዕክት የመስቀል በዓል የአንድነት እና የብርሃን ምልክት መሆኑን በመግለጽ ህዝበ-ክርስቲያኑም ይህን አብነት ይዞ ከመለያያት ይልቅ መተሳሰብን፣ ከአፍራሽነት ይልቅ ለአገር ዘብ መሆን ማስቀደም አለበት ብለዋል።

አገራችንን አሁን የገጠሟትን ፈተናዎችን አልፋ ወደምትታወቅበት ሰላምና መረጋጋት እንድትመለስ አብሮነትን በማስረጽ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ እና የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ ቤቴክርስቲያኗ ምዕመኑን አስተባብራ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

May be an image of one or more people, people standing and outdoors

አምባሳደር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው “መስቀል ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር፣ የአገራችን ስም በበጎ በማስጠራት፣ ባህላችን በማስተዋወቅ እና አንድነትን በማጠናከር ረገድ የበዛ ትሩፋት ያለው፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያከብሩት የአንድነትና የመተሳሰብ ምሳሌ እና በመላው ዓለም ደምቀን የምንታይበት ትልቅ በዓል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንድ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የአገር ህልውናችን ለማጽናት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

አገራችን በአሁኑ ወቅት በጽኑ የምትፈልገውን አንድነት፣ ተከባብሮ የመኖር እሴቶች፣ ድጋፍ የሚሹትን በመደገፍና የተጎዱትን በማጽናናት ቤተክርስቲያኗ የጀመረችውን አኩሪ ስራ አጠናክራ እንድትቀጥልም አምባሳደር ስለሺጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም