በዓሉን ስናከብር ለሰላም፣ ለአብሮነትና ልማት መጎልበት በመነሳሳት ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ

224

ሐረር/ጭሮ/ ጅማ/ ሻሸመኔ/ ግምቢ ፤ መስከረም 16/2015(ኢዜአ) የደመራና መስቀልን በዓልን ስናከብር የእምነቱ ተከታዮች ከሌሎች ወገኖች ጋር አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላም፣ ለአብሮነትና ልማት መጎልበት በመነሳሳት ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ።

የደመራ በዓል ደማቅ በሆነ ሥነ- ሥርዓት የእምነቱ ተከታዮችና ሌሎች በተገኙበት በኦሮሚያና ሐረሪ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች መከበሩን የኢዜአ ሪፖርተሮች ከየሥፍራው ዘግበዋል።

ሥነ-ሥርዓቱ በሐረር ከተማ በተከበረበት ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሳለኝ ባስተላለፉት መልዕክት ወጥቶ መግባትም ሆነ በዓላትን ማክበር የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ለሀገር ሰላም ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር ከፅንፈኝነት እና ዘረኝነት በመራቅ ሰላምን እና አብሮነትን በማጎልበት እርስ በእርስ በመረዳዳት ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጉዞ በሚያስቀጥል መልኩ መሆን አለበት ሲሉም መክረዋል፡፡

የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና የሀገሪቱ ሰላም በአስተማማኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለፈጣሪ በመፀለይ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ክልሉን በመወከል በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ነገዮ፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም የፍቅር እና የብልፅግና እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲከብሩ ከሌሎችም ወገኖች ጋር አንድነታቸውን በማጠናከር ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ሠላም፣ አብሮነትና ልማት መጎልበት በመነሳሳት ሊሆን እንደሚገባ ተመልክቷል።

አቶ ጌቱ፤ በአሁኑ ወቅት በሐረሪ ክልል የሠፈነውን ሰላም እና መረጋጋት በማስቀጠል በዓሉን በአብሮነት በማክበር አንድነታችንን ለኢትዮጵያ ጠላቶች የምናሳይበት ነው ብለዋል ፡፡

የሃይማኖት አባቶችም ተከታዮቻቸውን በበጎ ስነ ምግባር በመቅረፅ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

በደመራው በዓል ከታደሙት መካከል አቶ መላኩ አያሌው በሰጡት አስተያየት፤ የደመራና የመስቀል በዓልን በሀገሪቱ ሰላም እንዲስፍን ፈጣሪን በመለመን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በሀገሪቱ ላይ የከፈተውን ጥቃት ለመመከት በግንባር እየተወዳቀ ለሚገኘው ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ደጀን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓሉ በምዕራብ ሐረርጌ ጭሮ ከተማ ሲከበር ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ፤ ኢትዮጵያዊ አንድነትንና አብሮነትን ከሚያንፀባርቁ የጋራ እሴቶቻችንን ማሳያዎች አንዱ የመስቀል ደመራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከክብር በዓሉ ታዳሚዎች ወጣት ቤዛ ከተማ ፤ ሀገራችን ሰላሟ ተረጋግጦ ህዝቡ የነበረው አንድነት ተመልሶ ማየት እንመኛለን ብላለች፡፡  

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡትን የአንድነትና አብሮነት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴቶቻችን አጠናክሮ መቀጠል አለብን ስትል አስተያየት ሰጥታለች፡፡ 

አቶ ካሳሁን የሻነው በበኩላቸው፤ የደመራ መስቀል በዓል ሀገር ሰላም የመሆን ጉዳይ እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን የተመለከትንበት ነው ብለዋል፡፡

በጭሮ ከተማ በዓሉ በእኛነት ስሜት የደመቀ ነው ሙስሊም ወንድሞቻችን የአካባቢ ፀጥታን በማስከበሩ እየተባበሩን ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ 

ወይዘሮ ለምለም ጌታቸው በበኩላቸው የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የሚሰባሰቡበት ደማቅ የጋራ ሆኖ አይቸዋለሁ ብለዋል፡፡ 

የሀገራችን ሰላም የሚረጋገጥበት በዓል እንዲሆንልንም እንመኛለን ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

 በተመሳሳይ በጅማ፣ በሻሸመኔና በግምቢ ከተሞች የደመራ በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት መከበሩን የኢዜአ ሪፖርተሮች ከየሥፍራው ዘግበዋል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት( ዩኔስኮ) መዝገብ በዓለም ቅርስነት የሰፈረው የመስቀል ደመራ ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያዊያን የጋራ በዓል ነው፡፡