አሸባሪው ሕወሓት የሰብአዊ ርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀሙን ቀጥሎበታል-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

138

መስከረም 16 /2015 (ኢዜአ)አሸባሪው ሕወሓት የሰብአዊ ርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀሙን ቀጥሎበታል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ::

የመግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል:-

መንግሥት ተገዶ የገባበትን የትግራይን ጦርነት በሰላም ለመቋጨትና ለክልሉ ዜጎችም ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ በርካታ ጥረቶችን ሲያደረግ ቆይቷል።ተግባራዊ ርምጃዎችንም ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል።

በአንፃሩ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከዚህ ቀደም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ የተገኘ እርዳታን ለማድረስ ወደ ትግራይ ክልል የገቡ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት አላማ ሲጠቀምባቸው መቆየቱን መንግሥት በተደጋጋሚ ገልጧል።

ርዳታውንም ለታጣቂዎቹ ግብአት ሲያደርግ እንደነበር ተጋልጧል።ዓለም አቀፍ ተቋማት በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙና ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሱ ወንጀሎችን የማስቆም ኃላፊነት አለባቸው።

እንዲሁም ወደ ክልሉ የሚገባ ድጋፍ ለተገቢው አላማ መዋሉን የማረጋገጥ ግዴታም ተጥሎባቸዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ የርዳታ ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ መንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል።

የህወሃት የሽብር ቡድን ሦስተኛ ዙር ወረራ መፈፀሙን ተከትሎ መንግሥት የሃገርን ህልውናና የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር የመከላከል ርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።

መንግሥት የመከላከል ርምጃ ከሚወስድባቸው አካባቢዎች የርዳታ ድርጅቶቹ ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ መንግሥት በድጋሚ ያስጠነቅቃል።

የሽብር ቡድኑ ቀደም ሲል ካገታቸው የሰብአዊ ርዳታ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ በሥሩ የነበሩትንም የዓለም ምግብ ድርጅት እና የተመድ ዓርማ በመቀባት የጦር መሣሪያና ተዋጊዎችን በማመላለስ ለወታደራዊ ዓላማ እየተጠቀመ መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የርዳታ ድርጅቶች ለርዳታ የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች በአሸባሪው ቡድን ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን እንዲያረጋግጡ መንግሥት በጥብቅ ያስገነዝባል ።መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም