በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት እየተሰራ ነው--ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ

204

ባህር ዳር መስከረም 16/2015  (ኢዜአ) በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ አውቶሞቢሎችንና ባሶችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠምና ከውጭ በማስገባት ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚንስትር ገለጹ።

በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪን ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አውደጥናት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በአውደጥናቱ ላይ የተሳተፉት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚንስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዳሉት ዓለም የደረሰበትን እውቀት፣ አሰራርና የመሰረተ ልማት ደረጃን በመጠቀም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ዘርፉም የሚፈለገውን እድገት ለማስመዝገብ ችግሮችን በጥናት በመለየት ፖሊሲና ስትራተጅ ተቀርጾ ወደሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በ60 ከተሞች ሞተር አልባ ትራንስፖርቶችን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ 10 ዓመታት 148ሺህ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውቶሞቢሎችን እና 4ሺህ 800 ባሶችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ጨምሮ ከውጭ በማስገባት ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

"ይህን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስትራተጅ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማሳካት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት የያዘው ግብ የሚበረታታ ነው" ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት የሀገርን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት በመደገፍ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጾ እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል።

May be an image of 1 person and standing

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፣ ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ሃብት አመቺነት በመጠቀም ለአረንጓዴ ትራንስፖርት ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

"በቀጣይ በከተማዋ የሚሰሩ የአስፓልት መንገዶች እንደ ብስክሌትና ሌሎች ትራንስፖርቶችን ግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጧል" ብለዋል።

ከባህር ዳር ጢስ ዓባይ ያለው የአስፓልት መንገድና አዲሱ የዓባይ ድልድይ እነዚህን አካተው እየተገነቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ በር ተነስቶ እስከ ፖሊ ያለው ጎዳና የሳይክል መስመርን አካቶ ዳግም እንዲሰራ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመስማማት ዲዛይን ተጠናቆ ወደተግባር ሊገባ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከተማዋ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ሞተር ሳይክሎችና መኪኖች ምቹ በመሆኗ በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጡ ባለሃብቶች በከተማ አስተዳደሩ በኩል አስፈላጊው ትብብርና ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

"የባህር ዳር ከተማንም ሆነ ሌሎች የአገራችን ከተሞችን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው በሰው ሃይል አቅርቦትና በምርምር የበኩሉን ይወጣል" ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ናቸው።

"ዩኒቨርሲቲው በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪ ለመገጣጠም የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ካሪኩለም ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱ፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል" ብለዋል።

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን የሚገዙ ሰዎች ከታክስ ነጻ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የጉምሩክ ቀረጥም በቅናሽ መጠቀም የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩ በእለቱ በመድረኩ ላይ ተመልክቷል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም