በክልሉ የሚካሄደውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በግብአትና በቴክኖሎጂ ድጋፍ ይደረጋል- ሚኒስቴሩ

194

ባህርዳር መስከረም 16/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ዘንድሮው የሚካሄደውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በግብዓትና በቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚያደርግ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በክልል ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ትላንት በባህርዳር ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በመድረኩ ላይ እንዳሉት  በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንደ ክልል የተያዘው ግብ ሰፊ ቢሆንም ዕቅዱ እንዲሳካ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ዕገዛ ያደርጋል።

"ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ሃብት በማሰባሰብ እስከ 1 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ድጋፍ በማድረግ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዕቅዱ እንዲሳካ ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል።

የሚደረገው ድጋፍ ለግብዓትና ቴክኖሎጂ መግዣ፣ እንዲሁም ለድጋፍና ክትትል ስራዎች ማስፈፀሚያ እንደሚውል አመላክተዋል።

በተለይ ግብዓትን በተመለከተ አቅም በፈቀደ መልኩ ፈጥኖ ለማቅረብ  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ አክለው የፖለቲካ አመራሩ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የግብርና ምርምር ማዕከላት በዘርፉ ባለፈው ዓመት ተቀናጅተው በመስራት ያሳዩትን መልካም ጅምር በቀጣይም አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"መስራትና መለወጥ እንደምንችል ያለፈው ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ ትልቅ ማረጋገጫ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ "አርሶ አደሩን ከድህነት ለማላቀቅ በዕልህና በቁጭት ልንሰራ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው "በዘንድሮው የበጋ ወራት 250 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ለማልማት የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ሁሉን አቀፍ ርብርብ ይደረጋል" ብለዋል።

"ባለፈው ዓመት በህልውና ዘመቻ ውስጥ ሆነን በቅንጅት ያከናወንነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ እንደነበር ትልቅ ማሳያ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት ዘንድሮም የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ የፖለቲካና የግብርና አመራሩ እንዲሁም  ባለሙያው በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል።

"ክልሉንና ሀገሪቱን በዘላቂነት ከድህነት እናላቅ ካልን ሁላችንም በጊዜ የለኝም መንፈስ በዕልህና በቁጭት መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

እንደ ርእሰ መስተዳደሩ ገለጻ ያሉትን ትላልቅና አነስተኛ የመስኖ ግድቦችንና አማራጭ የመስኖ ልማት አውታሮችን ወደ ልማት ለማስገባት ተግባሩን ከአርሶ አደሩ ጋር ከወዲሁ የጋራ አድርጎ መጣር  ይጠይቃል።

ከዘንድሮ ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው ናቸው።

ለልማቱ 375 ሺህ ኩንታል ዘርና ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሚያስፈልገው ግብአት ውስጥ 300 ሺህ ኩንታል ዘርና ማዳበሪያ በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር በኩል እንደሚቀርብ ጠቅሰው ቀሪው በክልሉ በኩልየሚቀርብ መሆኑን አስታውቀዋል።

"የምግብ ዋስትናችንን በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ ለተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስኬት አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ለማድረግ ዝግጁ ነን " ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን አለምነው በበኩላቸው የቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን ጨምሮ 32 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት በዕቅድ መያዙን ተናግረዋል ።

ከአጋር አካላት ጋር ዕቅዱን የጋራ በማድረግ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባሻገር የሚለማውን መሬት የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በአማራ ክልል በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መኖሩን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም