የመስቀል በዓልን ስናከብር እንደ ሃገር የተደቀኑብንን ፈተናዎች በድል ለመወጣት አንድነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል፡- የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር

107

መስከረም 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) የመስቀልን በዓል ስናከብር እንደ ሃገር የተደቀኑብንን ፈተናዎች በድል ለመወጣት አንድነታችንን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማጠናከር ይጠበቅብናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሩ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የመስቀል በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በፍቅርና በአንድነት የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።

በዓሉ ያለው ለሌለው የሚለግስበት፣ የፍሰሃና የደስታ፣ መተሳሰብና አብሮነት የሚወደስበት ታላቅ በዓል ነው ያሉት፡፡

መስቀል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩ በክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለውን ፍቅር የገለጠበት፣ ለኋጢአት ይቅርታ፣ አንዲያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ቤዛ የሆነበት መስቀል የተገኘበትን ቀን በማሰብ ይቅርታና ምህረት የሚሰበክበት ልዩ በዓል በመሆኑ ይከበራል ብለዋል።

በ2014 ዓ.ም ያጋጠሙንን በርካታ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችን ወደ ቀደምት ባሕሉ እንዲመለስ ለማድረግ የሚያስችሉ ስርዓቶችን በአዋጅ በማስፀደቅ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

ጠንካራ ስርዓት ለመገንባት ቀደምት እሴቶች በትክክለኛ መንገድ መልሰን ማደራጀት በመጀመራችን ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች ማሳያዎች ናቸው ሲሉም ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

ክልሉ የሕዝቡን ባሕል ለማሳደግና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሁሉም መስክ የተጀመሩ ስራዎችና እየተገኙ ያሉ ውጤቶች የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ዕውን እንደሚያደርጉ የህዝባችን ተሳትፎና ተነሳሽነት አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሕዝባችን በሁሉም ዘርፍ እያደረገ ያለውን ሁለንትናዊ ተሳትፎውን ይበልጥ በማጠናከር እያስመዘገበ ያለውን ድሎች በማላቅ፣ የነገውን ተስፋ እውን ለማድረግ ባሕሉንና እሴቶቹን ጠብቆና ተንከባክቦ በጋራ ለመኖር ሕብረብሔራዊ ወንድማማችነትን ማጎልበት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የሀገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ከውጭና ከውስጥ የተቃጡብንን ጥቆቶች በጀግንነት በመመከት ላየ ያሉ የሃገር መከላከያ ሰራዊትንና ሌሎች የፀጥታ አካላትን እያደረጋችሁ ያለውን ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የደጀንነታችሁን ሚና በአግባቡ እንድትወጡ አደራ እያልሁ በዓሉ የሠላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የአንድነት እንዲሆንልን እመኛለሁ ነው ያሉት፡፡

የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ላዘኑት ፍቅራችንን በማሳየት፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ጎን በመቆም እንደ ሃገር የተደቀኑብንን ፈተናዎች በድል ለመወጣት አንድነታችንን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማጠናከር ይጠበቅብናልም በማለት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም