በዓሉ ለክልሉ ህዝብና ለመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆን እመኛለሁ- ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው

70

መስከረም 16 ቀን 2015(ኢዜአ) በዓሉ ለክልሉ ህዝብና ለመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆን የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ተመኙ።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የ2015 የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓሉ ለክልሉ ህዝብና ለመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው መስቀል በሁሉም አካባቢዎች የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የመከባበር እንዲሁም ይቅር የሚባባሉበት እሴታችን ደምቆ የሚታይበት በዓል ነው ብለዋል።

በመስቀል በዓል የተራራቁ ወዳጅ ዘመዶች በናፍቆት የሚገናኙበት፣ የቤተሰብ አባላት በአዲሱ ዓመት አዲስ እቅድ የሚያወጡበት እና ለላቀ ስኬት የሚተጉበት ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በክልላችን በአንዳንድ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ዘንድ የመስቀል በዓል የዘመን መለወጫ በዓል ጭምር በመሆኑ ከመስከረም 12 ቀን ጀምሮ በልዩ ልዩ ኩነቶች ደምቆ ይከበራል፤ ይህም በዓሉን ልዩ ስሜት የሚፈጥር ተናፋቂ በዓል አድርጎታል ብለዋል።

የተጀመረው የእድገት እና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በየአካባቢያችን ሰላማችንን አጽንተን ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም ሙሉ አቅማችንን እና ትኩረታችንን በልማት ላይ ልናደርግ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን አጠፋናት ሲሉ ይበልጥ እየፈካችና እየደመቀች የምትቀጥል፣ ሰበርናት ሲሉ ደግሞ የምትቃና ታሪካዊ ሀገር መሆኗን ዛሬም በጀግኖች ልጆቿ አስመስክራለች ማለታቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

የክልላችን ህዝብና መንግሥትም በአንድ በኩል ለጀግናው የመከላከያ ኃላችን ደጀን በመሆን በሌላ በኩል ሁላችንም በየተሰማራንበት የስራ መስክ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ልንረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም