ለኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ሰላም ማስተማር ማለት ለዓሣ ዋናን ለወፍ መብረርን ማስተማር ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

160

መስከረም 16 ቀን 2015(ኢዜአ) ለኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ሰላም ማስተማር ማለት ለዓሣ ዋናን ለወፍ መብረርን ማስተማር ነው፣ ‹ሰላም› ራሷ የኢትዮጵያ መንግሥት የከፈለላትን ዋጋ ያህል የከፈለላት የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመስቀል በዓልን በማስመልከተ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ደክመዋል ተብሎ ሲዘመትብን፣ በጽናት ቆመን አሳየን የትም አያደርሷቸውም የተባልንባቸው ፕሮጀክቶቻችን በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።

ይህ ሁሉ አልሳካ ሲል ደግሞ ትእግሥታችን እንደ ፍርሃት፣ ሰላም ፈላጊነታችን እንደ ድክመት ተቆጥሮ ሦስተኛ ዙር ጥቃት ተፈጸመብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ለሰላም የዘረጋነው እጅ ምንም ዋጋ ስላላገኘ ጦር እንዲይዝ እየተገደደ ነው" ሲሉ አመልክተዋል።

የታገሥነው በዚህም ሆነ በዚያ ወገን የሚያልቀው የእኛው ሕዝብ ነው በሚል ነውም ብለዋል።

ከጸብ ይልቅ ፍቅር ይሻላል ስንል ምላሹ እብሪት እየሆነብን ጭምር በንግግር ፋንታ ኃይል የመጠቀም ፍላጎት አላደረብንም ነው ያሉት።

ምንም እንኳን ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚመጣ ባይሆንም ከጦርነት በላይ ከሰላም እናተርፋለን ብለን እየተወጋንም ቢሆን ሀገር የሰላም እጆችን ከመዘርጋት እንዳልተቆጠበች ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው መንገዳችን ጨለማ፣ እግራችን ቄጤማ እንዲሆን ብዙ ተሠርቶብናል፤ ከድጡ ወደ ማጡ እንድንወርድም ያልተፈተለ ሤራ እንደሌለም አስታውቀዋል።

እንጀራችንን የበሉ ተረከዛቸውን አንሥተውብና ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወንዙ እንዲሞላብን፣ ጎርፉ እንዲደርስብን፣ ናዳ እንዲወርድብን ብዙ ተሠርቶ ነበር ሲሉም አክለዋል።

እንድንለያይ መዓት እየተወራ፣ የሕዝባችን አንድነት እንደ ብረት ጠንክሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደክመዋል ተብሎ ሲዘመትብን፣ በጽናት ቆመን አሳይተናልም ብለዋል።

የዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጭውም ትውልድ አደራ አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ የተነሣ ሀገራዊ ሕልውናችንን ለማስጠበቅ ስንል ወደ መከላከል እንድንገባ ተገድደናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከመጥፋት ለመታደግ፣ ሕዝብን ከብተና ለማዳን እና ሀገር እንደ ሀገር ቀጥላ የልጅ ልጆቻችን ሉአላዊት ኢትዮጵያን እንዲወርሱ ስንል የመጨረሻውን የመከላከል አማራጭ ወስደናል ሲሉም ተናግረዋል።

አሁንም እያደረግን ያለነው የመከላከል ውጊያ ይኼንን ታሪካዊ አደራ ለመወጣትና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ከአደጋ ለመከላከል ያሰበ ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ሰላም ማስተማር ማለት ለዓሣ ዋናን ለወፍ መብረርን ማስተማር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹ሰላም› ራሷ የኢትዮጵያ መንግሥት የከፈለላትን ዋጋ ያህል የከፈለላት የለም ብለዋል።

የገጠመን ወረራ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከሚፈለግብን በላይ አድርገናል ሲሉም መንግስት ለሰላም የሄደበትን ርቀት አሳይተዋል።

በዚህም ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሰላምን የሚመርጡት፣ ጦር ለመያዝ ስለማይችሉ አይደለም፤ ሰላምን ስለሚመርጡ ብቻ ነው በማለት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም