ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች

168

👉 ተሠውሮ የኖረው መስቀል የተገኘበትን በዓል የምናከብረው አስቸጋሪው የክረምት ወቅት ወጥቶ፣ የጠራውና አስደሳቹ የመጸው ወቅት ጀምሮ፣ የሞላው ወንዝ ጎድሎ፣ ፈታኙ ጭቃ ደርቆ፣ ጥሻው ተገልጦ፣ ጨለማውም በርቶ፣ ብርዱ ቀሎ፣ ሜዳና ተራራው በአበባ አጊጦ ባለበት በዚህ ወቅት ነው

👉 ኢትዮጵያውያን የሚያስተሣሥረን ገመድ ሊበጠስ የማይችል ጠንካራ መሆኑን አብዛኞቹ የሀገራችን ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላቸውን፣ ወይም ደግሞ የዓመቱን ታላቅ የምስጋና በዓላቸውን የሚያከብሩት በዚህ በመስከረም ወቅት መሆኑ ይታወቃል፤

👉 ይህም መነሻው አንዳች የጋራ ዕሳቤ እንደሚኖረው የሚጠቁም መሆኑ ለዚህም መነሻው የአንድነታችን፤ የአከባበሩ ልዩ ልዩ መሆን ደግሞ የኅብራዊነታችን ማሳያ ነው፤

👉 በዓላቱን የምናከብርበት መንገድ በአብዛኛው ተቀራራቢ ሲሆን ይህ ነገር በመላ ኢትዮጵያ ተመሳስሎና ተቀራርቦ ሲከበር ስናይ፣ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገራችን የተሣሠረችበትን ውስጣዊ ሥር እንድንመረምር የሚይደርግ ሃል አለው፤

👉 መንገዳችን ጨለማ፣ እግራችን ቄጤማ እንዲሆን ብዙ ተሠርቶብናል፣ ከድጡ ወደ ማጡ እንድንወርድ ያልተፈተለ ሤራ አለመኖሩን፣ እንጀራችንን የበሉ ተረከዛቸውን በእኛ ላይ ማንሳታቸውን፣ ወንዙ እንዲሞላብን፣ ጎርፉ እንዲደርስብን፣ ናዳ እንዲወርድብን ብዙ ቢሰራብንም የኢትዮጵያ አምላክ ግን አሳልፎ ስላልሰጠን በአስቸጋሪና በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈን እዚህ ደርሰናል፤

👉 ስለ ረሃብ እየተነገረብን፣ ምድሪቱ አትረፍርፋ እንደሰጠችን፤ ስለ በረሃማነት እየተሟረተብን ሀገራችን አረንጓዴ መልበሷን፤ ስለ ኪሣራ እየተለፈለፈ፣ ኢኮኖሚያችን ፈተናዎቹን እየተሻገረ መቀጠሉን፤ ከግራ ከቀኝ እየተዋከብን ሦስተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ ሞልተን ተርባይናችንን ማስነሳታችንን፤ እንድንለያይ መዓት እየተወራ፣ የሕዝባችን አንድነት እንደ ብረት መጠንከሩን፤ እንደ አልማዝም ባብራቱን፤ ደክመዋል ተብሎ ሲዘመትብን፣ በጽናት ቆመን ማሳያታችን፤ የትም አያደርሷቸውም የተባልንባቸው ፕሮጀክቶቻችን በመጠናቀቅ ላይ ናቸው፤

👉 ይህ ሁሉ አልሳካ ሲል ደግሞ ትእግሥታችን እንደ ፍርሃት፣ ሰላም ፈላጊነታችን እንደ ድክመት ተቆጥሮ ሦስተኛ ዙር ጥቃት ተፈጽሟል፤

👉 እነሱ ሲከፉ እኛ የለዘብነው፣ የአንድ ሀገር መንግሥትና የአንድ ሀገር ዐመጸኛ እኩል ለሕዝብ አያስቡም በሚል ነው፤

👉 ከጦርነት በላይ ከሰላም እናተርፋለን ብለን እየተወጋንም ቢሆን የሰላም እጆችን ከመዘርጋት አልተቆጠብንም፤

👉 የገጠመን ወረራ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከሚፈለግብን በላይ ማድረጋችን፤

👉 አሁን እያደረግን ያለነው የመከላከል ውጊያ ያለብንን ታሪካዊ አደራ ለመወጣትና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ከአደጋ ለመከላከል ያሰበ ነው፤

👉 ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሰላምን የሚመርጡት፣ ጦር ለመያዝ ስለማይችሉ አይደለም፤ ሰላምን ስለሚመርጡ ብቻ ነው።

👉 ለሰላም የዘረጋነው እጅ ምንም ዋጋ ስላላገኘ ጦር እንዲይዝ እየተገደደ ነው።

👉 በተለያዩ አካባቢዎች፣ በከተማና በገጠር፣ በአርሶና በአርብቶ አደር መንደሮች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር፣ በመሐልና በግንባር ሆናችሁ የብርሃነ መስቀሉን በዓል ለምታከብሩ ሁሉ፤ አንድ ነገር ላረጋግጥላቸሁ እወዳለሁ። ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በሁለት እጆቿ እየሠራች ፈተናዋን ትሻገረዋለች።

👉 በአንድ እጇ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚገባ አስጠብቃ ችግሯን ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ትታገላለች። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባችን በወዙ ጎተራው እንዲሞላ፤ ምሳውን በብድር ሳይሆን ከራሱ ማሳ ዘግኖ እንዲመገብ የሚችልበትን ስትራቴጂ ነድፈን መንቀሳቀስ እንጀምራለን።

👉 ይህ ጉዞአችን “የሌማት ትሩፋት” ይባላል። ዓላማው በቀላል መንገድ ገበታችንን በተመጣጠነ ምግብ መሙላት ነው።

👉 የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቀላል የዶሮ ርባታ፣ ቀላል የወተት ላሞች ርባታና የዓሣ ርባታን ይይዛል። አሁን ያለንበት ዘመን በአነስተኛ ቦታዎች፣ ቀላል ቴክሎጂዎችን በመጠቀም፣ በምግብ ራሳችን ለመቻል የሚያስችሉ ዕድሎች የተፈጠሩበት ዘመን ነው።

👉 ታላላቅ የእርሻ መሬት የሌላቸው ሀገሮች ይሄን መንገድ ውጤታማ ሆነውበታል። አረንጓዴ ዐሻራን ውጤታማ እንዳደረግነው ሁሉ፣ ወገባችንን አሥረንና እጅጌያችንን ሰብስበን ጎተራና ማጀታችን እንዲሟላ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ታጥቀን እንሠራለን።

👉 የመስቀል በዓል ያለፈውን ፈተና የምናስወግድበትና ለመጪው ተስፋ የምንሰንቅበት ነው። የአከባበሩ ሥነ ሥርዓትና የሽማግሌዎች ምርቃት ይሄንን ያሳየናል።

👉 ኢትዮጵያም በዚህ ዓመት የከረሙ ችግሮቿን እንድትፈታና ገበታዋን ለልጆቿ በሚያስፈልጋቸው ምግብ እንድትሞላ፣ ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ቆርጠን እንድንነሣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም