የልማት ተነሺዎችን ለመደገፍ በትኩረት እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

92
ሀዋሳ መስከረም 10/2011 በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከይዞታቸው የሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በትኩረት እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከይዞታቸው ለተነሱ የአርሶአደር ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ በድጋፍ አበርክቷል ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ጉዳዮች ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ይልማ በላቸው መንግስት የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠን ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል ። "በአፍሪካ ደረጃ ሞዴል የሆነው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማስፋፊያው አንድ አካል ነው" ያሉት ምክትል ስራ አስፈጻሚው ለሀገሪቱ እንዲሁም ለከተማዋና አካባቢዋ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት ላይ ባሉና ተገንብተው ወደ ስራ በገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ከይዞታቸው የተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ። በፓርኮቹ ግንባታ ሂደት በርካታ የልማት ተነሺዎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ለአብነት የገለፁት አቶ ይልማ ወደ ስራ በገቡ ኢንዱስትሪዎችም ተነሺ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ የስራ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋቱን ጠቅሰዋል ። ኮርፖሬሽኑ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተገነቡባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ላሉ የልማት ተነሺዎች ለልጆቻቸው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል ። የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ በበኩላቸው ፓርኩ በፈጣን እድገት ላይ አንደሚገኝና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር እያገዘ መሆኑን ገልፀዋል ። "ፓርኩ ከ20ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል" ያሉት ስራ አስኪያጁ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለፓርኩ ግንባታ ከይዞታቸው ለተነሱ 350 ለሚሆኑ የአርሶ አደር ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል ። "ለተማሪዎቹ በድጋፍ የተበረከቱት ቁሳቁሶች ከ200ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገዙ ናቸው " ብለዋል ። ሃዋሳ ከተማ አስተዳደርን ወክለው በድጋፍ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት አቶ በላይ ሃሜሶ በበኩላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለሃገሪቱ፣ ለክልሉና ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን በመግለፅ "ለልማት ተነሺ ልጆች የተደረገው ድጋፍ ወገናዊነትን ያመላከተ ነው" ብለዋል። ከልማት ተነሺ አርሶአደሮች መካከል አቶ መለቆ ቴማ ለልጆቻቸው በተደረገው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸው ገልፀዋል ። እንደ አቶ መለቆ ገለጿ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው የፓርኩ ይዞታ ተለውጦ በማየታቸው ኩራት ተሰምቷቸዋል ። የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ጥበቡ ወታንጎ የተበረከተለት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በትምህርቱ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠቃሚና መነሳሳት የፈጠረለት መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም