ከተማ አስተዳደሩ ለመካለከያ ሰራዊቱ ድጋፍ አደረገ

138

ደብረ ማርቆስ መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ስንቅ ድጋፍ አደረገ።

የከተማ አስተዳደሩ ተወካይ አቶ አስቻለው አዳነ እንዳሉት የህወሃት የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ወረራ እየመከተ ላለው የመከላከያ ሰራዊት እገዛ ማድረግ ተገቢና ግዴታ ነው።
የመንግስት ሰራተኛው ከደሞዙ፣ ነጋዴው ደግሞ ካለው በማዋጣት፣ የደብረ ማርቆስ ከተማ ህዝብ በሚችለው አቅም በማዋጣት የአገሪቷን ሉዓላዊነት በማስከበር ላይ ለተሰማራው ሰራዊት ደጀንነቱን እያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።

በዛሬው እለትም ለመከላከያ ሰራዊቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው 43 ሰንጋዎችንና 187 ኩንታል በሶ ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት።

የደብረ ማርቆስ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ደጀንነት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ድጋፉን በዋግ ግንባር የተረከቡትና በግንባሩ የመከላከያ ሰራዊት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አስተባባሪ ሌተናል ኮሎኔል ታጠቅ ንጉሴ እንዳሉት ሰራዊቱ የተቃጣበትን ጦርነት እየመከተ የጠላትን ህልም እያጨለመ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለው የደጀንነት ሚናም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ህዝብም በዛሬው እለት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ መሰል ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በዚሁ ግንባር ለሚገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ስንቅ ቀደም ሲል ድጋፍ ማድረጉም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም