የኡጋንዳው ሞደርን እግርኳስ ቡድን ተጫዎቾች የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስትን ጎበኙ

196

ጎንደር መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) ''የአፍሪካ ተምሳሌት የሆነችውንና የበርካታ የብዝሃ ባህል፣ እምነትና ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ በመጎብኘታችን አስደስቶናልናል'' ሲሉ የኡጋንዳው ሞደርን እግርኳስ ክለብ ተጫዎቾች ተናገሩ።

19 አባላትን ያካተተው የኡጋንዳው ሞደርን እግርኳስ ክለብ ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት በፋሲለደስ ስቴዲየም ከፋሲል ከነማ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያካሄዳሉ።

የክለቡ አባላት ከግጥሚያው በፊት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት ዛሬ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የክለቡ አባለት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በርካታ ሃይማኖቶችና ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር ነች።

የእግር ኳስ ክለቡ አሰልጣኝ ሚስተር ዋሳዋ ቤቦሳ "ኢትዮጵያ ጥንታዊ የሰው ዘር ቀደምት መገኛ ሀገር በመሆኗ የአፍሪካውያን እናት እና የኩራት መገለጫ ነች" ብለዋል።

ጥንታዊው የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግስት ኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ከመሰረቱ  ሀገሮች ግንባር ቀደም ታሪክ ያላት መሆኑን አስረጂ ነው ሲልም ምስክርነት ሰጥተዋል።

ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦችና ሀገራት የቆየ ወዳጅነት የሚያጠናክርና የአፍሪካን ስፓርት ወደ ከፍታ ለማደረስ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክለቡ ተጫዋች ካኮም አሚር በበኩሉ ኢትዮጵያዊያን እንግዳ አክባሪና ተቀባይ ህዝቦች ናቸው ነው ያለው።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብዝሃ ባህልና ሃይማኖት ባለቤትና እምነቶች ተከባብረውና ተዋደው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ተረድቻለሁ ብሏል።

''ኢትዮጵያ ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ያላት ዋነኛ የምስራቅ አፍሪካ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ነች'' ያለው ደግሞ የክለቡ ምክትል አምበል ኪያምባ ኢብራሂም ነው።

ወደ ሀገሬ ስመለስ ስለ ኢትዮጵያ መልካም ገፅታ ለወዳጆቼና ጓደኞቼ  አስረዳለሁ ሲልም አስታውቋል።

የጎንደር ከተማ ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው የኡጋንዳው የስፖርት ክለብ ከተማውን መጎብኘቱ ከስፖርቱ ባሻገር የአካባቢውን የቱሪስት መስህቦች ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም