በሐረር ከተማ ደረቅ ቆሻሻ የጤና ችግር እያስከተለ መሆኑን የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ

58
ሀረር መስከረም 10/2011 በሐረር ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተከማቸ የመጣው የደረቅ ቆሻሻ በህብረተሰቡ ላይ የጤና ችግሮች እያስከተለ መሆኑን የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ። በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኘው ደረቅ ቆሻሻ እያስከተለ ባለው ማህበራዊ ችግርና መፍትሄው ላይ በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ዮኒስ እንደገለጹት በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ላለፉት ሦስት ወራት የተከማቸው ደረቅ ቆሻሻ በወቅቱ ባለመወገዱ በነዋሪው ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር እያስከተለ ነው። በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት እንደ አተት ያለና ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ የጤና ችግሮች ያጋጠማቸው ከ20 በላይ ህሙማን ወደ ተለያዩ ጤና ተቋማት መጥተው የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣው የጤና ችግር እየተስፋፋ ከመጣ በቂ የጤና ባለሙያና የመድኃኒት አቅርቦት ዝግጅት አለመኖሩንም አቶ ኤልያስ አያይዘው ጠቁመዋል። ወቅቱ ትምህርት የሚጀመርበት በመሆኑ ደረቅ ቆሻሻው በህጻናት ላይ ከፍተኛ የጤና እክል ሊያመጣ እንደሚችል የጠቆሙት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አፈንዲ አብዱልዋሲ ናቸው። በአሁኑ ወቅት  በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሳይቀር ደረቅ ቆሻሻ እየተከማቸ መምጣቱን ተናግረው በቆሻሻ አወጋገድ ላይ እየተስተዋለ ያለው ችግር ፈጥኖ እልባት ሊያገኝ እንደሚገባ ገልጸዋል። የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ መሀመድ ኑረዲን በበኩላቸው " ከከተማው ተሰብስቦ ለሚጣለው ቆሻሻ አርሶ አደሩ ከሚጠይቀው ካሳ አንጻር ችግሩን መፍታት አልተቻለም " ብለዋል። ችግሩ ከቢሮው አቅም በላይ መሆኑንና ሕብረተሰቡ ከካሳና ተያይዞ የሚያነሳቸውን መሰል ጥያቄዎች አመራሩ ሊፈታው እንደሚገባ አመልክተዋል። የክልሉ አፈ ጉባዔ አቶ አብዱማሊክ በከር በበኩላቸው " ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አመራሩ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት ይሰራል" ብለዋል። በተለይ ከአርሶ አደሩ ጋር የሚታየውን አለመግባባትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በጥናት የተደገፈ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ችግሩን በጊዜያዊነት እንዲፈታም የወረዳ አመራር፣ ህብረተሰቡና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሳተፍ ቆሻሻ በአቅራቢያ ማስወገድ በሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረት መደረግ አንዳለበት አሳስበዋል። በከተማው ከጊዜ ወደጊዜ እየተከማቸ በመጣው ቆሻሻ በህብረተሰቡ ላይ እየተከሰተ የሚገኘውን የጤና ጠንቅ ኢዜአ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም