ሁሉም አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከአሁን በፊት የገቡትን ቃል ወደ ተግባር እንዲለውጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ

92

መስከረም 14 /2015 (ኢዜአ) ሁሉም አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከአሁን በፊት የገቡትን ቃል ወደ ተግባር እንዲለውጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ::

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 77ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ንግግር አድርገዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በአሁኑ ወቅት ዓለም በበርካታ ፈተናዎች እያለፈች መሆኗን ተናግረዋል ።

የአየር ንብረት ለውጥ፣የከፋ ድህነት፣ግጭትጨ፣ሽብርተኝነት እና ጂኦ ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች የባለብዙ ወገን የግንኙነት መድረክን እየፈተኑት መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ ደመቀ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ችግር እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል ።

አሁን ላይ በቀጣናው የተከሰተው ከባድ ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አንስተዋል።

ሁሉም አገራት ከአሁን በፊት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ለመቋቋም የገቡትን ቃል ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አገራቱ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን ለመቀነስ የተገባው ቃል ወደ ተግባር መቀየር ይገባዋል ነው ያሉት።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለመከላከል አሰፈላጊውን ፋይናንስ መመደቡ ላይም በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይገባናል ነው ያሉት።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት አስቀድሞ በመተንበይ ለመከላከል እና ለመቋቋም በትብብር መስራት ይገባናል ብለዋል።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሆኑ በካይ ጋዝ ልቀት ያላት ድርሻ ከቁጥር የማይገባ ቢሆንም ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዟችን ለመቀነስ ግን የተለያዩ ስራዎችን እየከወነች መሆኑን አንስተዋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንስተዋል።በዚህ መርኃ ግብር በበርካታ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸውን ያነሱት አቶ ደመቀ አሁን ላይ ጠንካራ የደን ተከላ ባህል ማዳበር መቻሉን ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የኢነርጂ ሽግግር እና የአረንጓዴ እድገት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

ይህ ተግባሯም እውቅና እና ተግባራዊ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል ብለዋል።አቶ ደመቀ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጠይቀዋል።አፍሪካዊያን ጥያቄያችን ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ሁልጊዜም ይህን ጥያቄ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን የሚችለው የሚሰጠውም በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ተገቢው ውክልና ሲኖራት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በማኅበራዊ ፣ ምጣኔ ሀብት እና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለውጥ ማሳየቷን የተናገሩት አቶ ደመቀ፤ እንደ አገር ህልውናዋን የሚፈታተኑ ችግሮችም እንዳጋጠሟት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የሕወሐት ቡድን እ.ኤ.አ በህዳር 2020 ላይ በሰሜን ዕዝ ላይ የከፈተውን ጥቃት ተከትለው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች መሆኑን አንስተዋል ።

የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በሚደረግ የሰላም ድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ ነው ብለዋል::

ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ የሚደረግ ሌላ አካሄድ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር በሚደረግ የሦስትዮሽ ድርድር ጉልሕ ተፅዕኖ በማያደርስ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት በማድረግ ልዩነቶችን ለመፍታት አሁንም ፅኑ አቋም አላት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም