ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ሀገራዊ ግብ ለማሳካት በየአካባቢው የግብርና ልማት አቅምን ወደውጤት መቀየር ይገባል-ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

128

ሀዋሳ መስከረም 14/2015 (ኢዜአ)--ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ ያስቀመጠችውን ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት የየአካባቢውን የግብርና ልማት አቅም ወደ ውጤት መቀየር ይገባል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።

በደቡብ ክልል በመኸር እርሻው እየለማ ካለው ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ከ53 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የፌዴራል እና የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመኸር አዝመራ እየለማ ያለውን ሰብል ዛሬ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በአመራሮቹ ከተጎበኙ አካባቢዎች መካከል በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ሶሎቄ ቀበሌ በ500 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የለማው የስንዴ አዝመራ ይገኝበታል።

በጉብኝቱ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ስንዴ ከራሷ አልፋ ወደውጭ መላክ የሚያስችል አቅም እንዳላት በተግባር ፍንጭ እየታየ ነው።

"ይህንን ሀገራዊ ራዕይ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ በየአካባቢው ያለውን የግብርና ልማት አቅም ወደ ውጤት የሚቀይሩ ተግባራትን ማከናወን ይገባል" ሲሉም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

ስንዴ ወደውጭ የመላክ ዕቅድ እንዲሳካ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው፣ በተለይ የተደራጁ አርሶ አደሮችን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል

ኢንጂነር አይሻ እንዳሉት፣ ኩታገጠም የእርሻ ዘዴ ከመንግስት አካላት አስተሳሰብ ወጥቶ የህዝብ እንዲሆን ማድረግ በመቻሉ በአሁን ወቅት በተለይ ሴት አርሶ አደሮች በዚህ ሥራ ላይ እያደረጉ ያሉት ተሳትፎ እንደ ሀገር ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

"የአካባቢው አርሶ አደሮች የውሀ አማራጮችን ተጠቅመው በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት እንዲችሉ ከክልልና ከዞን የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመስኖ ፕሮጀክቶችን በጥናት ለመገንባት በትኩረት እንሰራለን" ሲሉም ገልጸዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ "የአካባቢው አርሶ አደሮች በኩታገጠም ያለሙት ሰብል ከተባበሩ አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው" ብለዋል።

በርካታ ሴቶች በኩታገጠም የእርሻ ልማት በግንባር ቀደምትነት ተሳትፈው ያስመዘገቡት ውጤት እስከዛሬ ያላቸውን አቅም በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለ የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሴቶችን ግንባር ቀደም የልማት ተዋናዮች ለማድረግ የትምህርት፣ የቴክኖሎጂና ሌሎች እገዛዎችን ለማድረግ እንደሚሰራም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በክልሉ በተያዘው የመኸር እርሻ በአዝዕርት፣ በአትክልት እና ሌሎች ዓመታዊ ሰብሎች ከ1 ሚሊዮን 87 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ53 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከ887 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል መሸፈኑንና ምርታማነትን ለማሳደግ 750 ሺህ ኩንታል የግብርና ግብአቶች ለአርሶ አደሩ መቅረባቸውን አስረድተዋል።

አቶ አድማሱ እንዳሉት በአሁን ወቅት የበልግ ሰብል ዘግይቶ የሚደርስባቸውና በዝናብ እጥረት ምክንያት ወደኋላ ቀርተው የመኸር ሥራ በጀመሩ አካባቢዎች ላይ ዘር የመሸፈን ሥራ እየተከናወነ ነው።

ቀድሞ በዘር በተሸፈነ መሬት ላይም የማሳ እንክብካቤ እንዲሁም የተባይና በሽታ ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በኩታ ገጥም እርሻ ዘዴ ስንዴ እያለሙ ካሉ ሴት አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ሳራ ግዛው በ500 ሄክታር መሬት ላይ 142 ሴቶች እና 210 ወንዶች ተደራጅተው እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በልማቱ የበረታው ደካማውን በመደገፍና በማገዝ ተባብረን በመስራታችን ለእዚህ በቅተናል" ነው ያሉት። 

"በትራክተር፣ በኮምባይነር እንዲሁም በሌሎች ቴክኖሎጂዎች አቅርቦቶች ላይ መንግስት እገዛ ቢያደርግልን ጉልበትና ጊዜ ቆጥበን ከእዚህ በበለጠ ማምረት እንችላለን" ሲሉም ወይዘሮ ሳራ ገልጸዋል።

ማሳቸውን በኩታገጠም ማልማታቸው የዘር፣ የማዳበሪያና ሌሎች አቅርቦቶችን በአግባቡና በወቅቱ ለመጠቀም እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ዳርሰማ ሽጉጤ ናቸው።

"በእዚህም በተናጥል ከማለማው የተሻለ ውጤት ሊሰጥ የሚችል አዝመራ ለማየት በቅቻለሁ" ብለዋል።

የመኸር አዝመራ የመስክ ምልከታው ከጉራጌ ዞን በተጨማሪ ሌሎች አካባቢዎችንም ያካተተ ሲሆን በስልጤ ዞን ምስራቅ ስልጢ ወረዳ በሚገኘው ትንሹ አባያ ሐይቅ ዙሪያ እየለማ ያለው የሙዝ እርሻም ተጎብኝቷል።

በመስክ ጉብኝቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፌዴራል አስከ ዞን አስተዳደር ያሉ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም