በሃዋሳ ከተማ በ80 ከሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሁለገብ የገበያ ማዕከል ሕንጻ ተመረቀ

139

ሃዋሳ (ኢዜአ) መስከረም 14 ቀን 2015 በሃዋሳ ከተማ በኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሁለገብ የገበያ ማዕከል ሕንጻ በከተማ እስተዳደሩ ምከትል ከንቲባ አቶ ሚልኪያስ ብትሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

የኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኩሪያ አየለ በምረቃው ላይ እንደገለጹት፣ ቢዝነስ ግሩፑ የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ ለማጠናከር በ1985 ዓ.ም የተቋቋመ ነው።

የኩባንያው አባላት በወቅቱ የነበራቸው ራዕይ ለሀገር ልማት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ በመሆኑ የኩባንያው የሥራ ዘርፎች ይህንን እውን ለማድረግ የሚያግዙ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

"በተለይ ኩባንያው ከዘመናዊ የተሽከርካሪ አቅርቦት ባሻገር የግብርና እና የማዕድን ውጤቶች ለውጭ ገበያ በመላክና በመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት ላይ በመሰማራት ውጤታማ ሆኗል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም “ሰላም ፋርማሲ” በሚል ስያሜ ስድስት የመድሃኒት መሸጫ ፋርማሲዎችን በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አንድ በመክፈት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን  አስታውቀዋል።

ኩባንያው የፋርማሲ አገልግሎቱን በሀዋሳ ከተማም ለመስጠት እቅድ እንዳለው ጠቅሰው፣ "የንግድ ሥራዎቹን ተደራሽነት ለማጠናከር በሃዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ጅማ እና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ ቅርንጫፎች ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ነው" ብለዋል።

ሀዋሳ ከተማ በፍጥነት እያደገች ከመሄዷ ጋር ተያይዞ ከአዲስ አበባ ውጪ የመጀመሪያ የሆነውን የኩባንያውን ዘመናዊ ሕንፃ በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱንም አስታውቀዋል።

የሕንጻው ግንባታ ለ10 ዓመታት ቢጓተትም በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለመሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ለተደረገው ትብብር አቶ መኩሪያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሃዋሳ ከተማ በ1ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ባለ አምስት ወለል ሁለገብ የገበያ ማዕከል ሕንጻ የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ጨምሮ ለባንክና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች እንዳሉት ተገልጿል።

ሲነሳ በ5 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን 460 ሚሊዮን ብር ለማድረስ እንደቻለ የገለጹት አቶ መኩሪያ፣ "ለ400 ዜጎችም የሥራ እድል ፈጥሯል" ብልዋል።

በሕንጻው የምረቃ ሥነ ስርዐት ላይ የተገኙት የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኮንስትራክሽን ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚልኪያስ ብትሬ በበኩላቸው፣ በሀገር ላይ የታየው ለውጥ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በባለሃብቶችና በህዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ጭምር የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የግሉ ባለሀብት የልማት ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁመው፣ የሃዋሳ ከተማን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የአስተዳደሩ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደማይለይ አረጋግጠዋል።

በከተማዋ ማዕከላዊ ቦታ ተገንብቶ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ሁለገብ የገበያ ማዕከል ሁሉንም ሥራ ያማከለ ከመሆን ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

በማህበር መደራጀት ውጤታማ እንደሚያደርግ በተግባር የታየበት በመሆኑ፣ የአክሲዮን ማህበሩ አባላት ሕንጻው የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የከተማ አስተዳደሩና የካቢኔ አባላት በአክሲዎን ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶችን እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ ሁሉንም መሰረተ ልማቶች አሟልቶ ባለሀብቶችን ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ መሆኑንም ምከትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም