ኀብረተሰቡ የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር ድንገተኛ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

98

መስከረም 14/2015 (ኢዜአ)  ኀብረተሰቡ የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር ድንገተኛ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ፡፡

በዓሉን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ የመስቀል በዓል በሰላም እና በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ከተማ አስተዳደሩ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በነገው እለትም የሃይማኖት አባቶች የሚሳተፉበት የጽዳት ዘመቻ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡

ውሃን ጨምሮ አስፈላጊ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆን በቅንጅት መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡

በበዓሉ ወቅት ድንገተኛ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ኀብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው ናቸው፡፡

ኀብረተሰቡ ደመራ በሚለኩስበትና ለበዓል ምግብ በሚያዘጋጅበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበው፤ ከሚሽኑ ለድንገተኛ እሳት አደጋ ቁጥጥር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስርጭት የቴክኒክ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው፤የደመራ ቦታዎች ከኤሌክትሪክ መስመሮች ቢያንስ 20 ሜትር መራቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ለበዓሉ ድምቀት የሚሆኑ የጎዳና ላይ ማስዋቢያዎችን በሚሰቀሉበት ወቅትም የኤሌክትሪክ መስመሮችን ታሳቢ ማድረግ አንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ለበዓሉ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ችግር እንዳያጋጥም በበቂ ሁኔታ ዝግጅት መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡በደመራ አከባበር ወቅት ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቢከሰት በነጻ የስልክ መስመር 939 በመደወል ማሳወቅ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም