“ያሆዴ” ክብረ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

103

ሆሳዕና ፤ መስከረም 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከታደለቻቸው በርካታ የአብሮነት መገለጫ ቱባ ባህሎች አንዱ የሆነው “ያሆዴ” በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

ሚኒስትሩ የሀድያ ብሄር የዘመን መለወጫ በሆነው የ2015 " ያሆዴ" ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ፤ ኢትዮጵያ በርካታ የአብሮነት መገለጫ የመሆኑ ቱባ ባህሎች የታደለች ናት።

May be an image of 9 people and people standing

ከነዚህም አንዱ "ያሆዴ" መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በዓሉ ሁሉም በደስታ የሚያከብሩት ፣ ለሀገር እድገትና ብልጽግና በተምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

ክብረ በዓሉ የመረዳዳትንና የዜጎችን የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር ረገድ እሴቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ በዓሉን በዓለም ቅርስነት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በሚኒስቴሩ የተለያየ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የያሆዴ ክብረ በዓል ባህላዊ ይዘቱን አስጠብቆ ለማስቀጠል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ነው ሚኒስትሩ ያመላከቱት።

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ ፤ የዘንድሮን በዓል በሀገር ደረጃ የገጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም በድል ያለፍንበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

May be an image of 2 people and people standing

አሮጌውን ዓመት በድል ያለፈ ተወላጅ በአካባቢው አባባል ከባለቤቱ ጋር የቆየች ነፍስ በያሆዴ በዓል ትጠግባለች በሚል ይታመናል ነው ያሉት።

በበዓሉ ዕለት እንኳን የሰው ልጅ እንሰሳት ጠግበው እንዲያሳልፉ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ከመሆኑም ባሻገር ለዜጎች ሰላምና አብሮነት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

"የብሄሩ በዘመን መለወጫነት የሚታወቀው "ያሆዴ"ክብረ በዓል ከአከባበር ይዘቱ ባለፈ ለሀገር ሰላምና አብሮነት መጠናከር ፈጣሪን ህዝቡ የሚማጸንበት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እርስቱ ናቸው።

ከዚህ አንፃር አዲሱ ዓመት የሰላም የብልፅግናና የእድገት እንዲሆን የሚታሰብበት በዓል ነው" ያሉት ኃላፊው፤ እሴቱ ሳይበረዝ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም