አዲሱ ስርዓተ ትምህርት አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን የወላጆችና መምህራን በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል

179

መስከረም 14 ቀን 2015 (ኢዜአ)  አዲሱ ስርአተ ትምህርት አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን የወላጆችና የመምህራን የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ "ትምህርት ለብዘሃ ባህልና ለሃገር ብልፅግና" በሚል መሪ ቃል 29ኛው ከተማ አቀፍ ትምህርታዊ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላት በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ቢሮው የትምህርት ጥራት ተግዳሮቶች ለመፍታት በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡

በ2014 የትምህርት ዘመን በተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ በዘርፉ የተሻለ ስራ መከናወኑን  ገልጸው፤ ለአብነትም በ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፣

ይህም ስራ በ2015 የትምህርት ዘመን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በማውጣት በመማርያ ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታ የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ችግር መፍታቱን አብራርተዋል፡፡

የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ-ግብሩም አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ከማድረጉም በላይ የስራ እድል መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

የትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ስራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅዊ አሰራር እንደሚጠይቅም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡

በዚህም የአዲሱ ስርአተ ትምህርት አተገባበር  ውጤታማ እንዲሆን የወላጆችና የመምህራን ብርቱ ቅንጅት  ያስፈልጋል ብለዋል። 

በቀጣይ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ትግበራ የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት መጽሃፍቶች ታትመው የሚሰራጩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መምህራን በአዲሱ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ከትርጉም ጀምሮ ቀን ከሌት በመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋይዛ መሃመድ በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች በእውቀትና በስነ- ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህን ለማሳካት ትምህርት ቢሮ በተማሪዎች ምገባ የትምህርት ቁሳቁሶች በማሟላትና መሰል ድጋፎች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለተማሪዎቹ ውጤታማነትም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጉባኤው የሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም የተመዘገቡ ውጤቶች፤የታዩ ድክመቶችና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በተጨማሪም በጉባኤው በ2014 የተሻለ አፈፃፀም ለነበራቸው የትምህርት ባለድርሻ አካላት የእውቅናና ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም