ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአካባቢ ጥበቃ ያከናወነቻቸውን ተግባራት በሚገባ ለማሳወቅ መዘጋጀት አለባት-ምሁራን

216

መስከረም 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአካባቢና ስነ ምህዳር ጥበቃ ያከናወነቻቸውን ተግባራት በሚገባ ለማሳወቅ መዘጋጀት እንዳለባት ምሁራን ገለጹ፡፡

አስተናጋጇ ግብጽ ጉባኤውን በዓባይ ወንዝ ላይ ካላት ሀሰተኛ ትርክት ጋር ለማያያዝ ልትሞክር ስለምትችል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የሰው ልጅ በተፈጥሯዊ መልኳ ላይ በግደሌሽነት በሚያሳርፍባት መጎሳቆል ሁለንተናዊ ገጿ እየተዘባ፣ መዘዟ እየበዛ መጥቷል።

ይህም ለሰው ልጅ ለራሱም ሆነ ለሌሎች ተፈጥሯዊ ሀብቶች ሕልውና እየተገዳደረ፣ የነበረውን አየር ንብረት እንዳልነበረ እያደረገ ዓለምን ስጋት ላይ ጥሏታል፡፡

የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የበርሃማነት መስፋፋት፣ የዝናብ መጠንና ወቅት መዛባት፣ ድርቅ፣ የውቅያኖስ ውሃ መጠን መጨመር፣ ጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ሰደድ እሣትና ሌሎች መዘዞች በርክተዋል።

ከጊዜ ጊዜ እየተባባሰ የቀጠለው የአየር ንብረት ለውጥ የሰውን ልጅ ሕይወት ከመቀየር አልፎ አያሌ የእንስሳትና የእጽዋት ዝርያዎችን ከምድረ ገጽ እየጠፉ መጥተዋል።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት በነዳጅ፣ በጋዝ፣ በድንጋይ በመጠቀም በሚያከውናቸው ተግባራት የሚለቀቀው የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ 50 በመቶ ጨምሯል።

የምድርን የሙቀት መጠን ከወዲሁ እልባት ካልተሰጠው ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አሁን ካለበት 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሸየስ ወደ 2 ድግሪ ሴልሺየስ ያሻቅባል የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ለሰው ልጆች ሕልውና ስጋት ለሆነው አየር ንብረት ለውጥ ላይ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ላይ ለመድረስ በተባበሩት መንግስታት አይነተ ብዙ መድረኮች ይደረጋሉ።

በዘርፉ በጉልህ ከሚጠቀሱ ጉባዔዎች መካከል አንዱ ከ100 በላይ የዓለም አገራት መሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ወይም 'ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ' ነው።

የመጀመሪያው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በፈረንጆቹ አቆጣጠር መጋቢት 1995 በጀርመን በርሊን ከተማ የተካሄደ ሲሆን ዘንድሮም ለ27ኛ ጊዜ በግብፅ አዘጋጅነት በሻርማልሸክ ከተማ ይካሄዳል።

ክዮቶ ፕሮቶኮልና የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተደረጉበት ይህ ጉባዔ፤ ዘንድሮውም በተለይም የአፍሪካ ጉባዔ አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደሚወሱ ይጠበቃል።

በዚህም ግብፅ የጉባዔው አስተናጋጅ አገር መሆኗን ተከትሎ ጉባዔውን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማያያዝ ፍላጎት ይኖራታል የሚሉ ወገኖች አሉ።

የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተመራማሪዎችና ሞጋጎችም ኢትዮጵያ በጉባዔው ላይ የሚጠበቅባትን በቂ ዝግጅት ካደረገች፤ በአየር ንብረት ላይ ያደረገችው እስካሁን ክንውኗ ለሌሎች አርዓያ እንደሆነ ዕድሉን ትጠቀማለች የሚል እምነት አላቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩና የውሃ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ኢትዮጵያ በአካባቢና ስነ ምህዳር ጥበቃ ላይ ምስጉን ስራ አከናውናለች ይላሉ።

የአረንጓዴ አሻራን መርሐ ግብርን ለአብነት ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ በሌላ በኩል በሕዳሴ ግድቡም ረገድ ዝናብ ሲወርድ እየሞላች ዝናብ ሳይኖር ሙሌቷን እያቆመች ለሁሉም ወገን በሚጠቅም አግባብ እየተራመደች መሆኑን ይገልጻሉ።

በዚህም ኢትዮጵያ በ27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ በመስኩ ያከናወነቻቸውን ተግባራት በሚገባ ለማስረዳት መዘጋጀት እንዳለባት ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና እስያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ተመራማሪውና የዓባይ ወንዝ ውሃ ጉዳይ ተሟጋቹ ዶክተር ሳሙኤል ተፈራም ግብጽ አጋጣሚውን ተጠቅማ የምታነሳቸው ትርክቶች እንደሚኖሩ ይጠብቃሉ።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግስትን ምሁራን ከወዲሁ ዝግጅት አጠናቀው ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም