ለህዝቦች ሰላምና አንድነት መጠናከር ምሰሶ የሆኑ የሀገሪቱን ባህላዊ እሴቶች መጠበቅ እንደሚገባ ተመለከተ

92

ሶዶ፤ መስከረም 14 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- ለህዝቦች ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር መጠናከር ምሰሶ የሆኑ የሀገሪቱን ባህላዊ እሴቶች መጠበቅ እንደሚገባ ተመለከተ።

የወላይታ ብሄር ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል ባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በሶዶ ከተማ ተካሂዷል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ ባደረጉት ንግግር፤ባህላዊ እሴቶቻችን የህዝቦችን ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክሩና የሚጠብቁ ምሰሶ ናቸው ብለዋል።

ከእነዚህ አንዱ የሆነው የወላይታ ብሄር የዘመን መለወጫ የ"ጊፋታ " በዓል የእርቅ መሰረትና የሰላም ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓሉን በቁርሾና ጥላቻ ማክበር የማይቻል መሆኑን እንደሚያውቁ ያወሱት  አቶ ተስፋዬ፤ በዓሉ የለውጥና የአዲስ መንፈስ ተምሳሌት በመሆኑ በልዩ ዝግጅት እንደሚከበር ተናግረዋል።

 ጊፋታ የህዝቦችን የሰላምና የአንድነት እሴት ያጠናክራል ብለዋል።

በተለይ እንደዚህ ያሉ  በዓላት ህዝቦችን ከማስተሳሰር ባሻገር ቀጣዩ ትውልድ ባህሉንና ማንነቱን እንዲሁም እሴቱን እንዲያውቅ ዕድል ስለሚፈጥሩ ሊጠበቁ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሰላምና አንድነት እንዲሁም አብሮነትና ተስፋን በማስያዝ ረገድ ለማህበራዊ ግንኙነት ምሶሶ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዓላቱ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ  ሁሉም አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመው፤ በታሪክ መሰነድና ለዓለም ማህበረሰብ እንዲተዋወቁ መስራት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የጊፋታን በዓል በዓለም በማይዳሰሱ ቅርሶች ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲያግዝ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አዲሱ ዓመት በሰላም፣ በፍቅርና በእርቅ በመቀበል የበዓሉን ዓላማ የሚያሳኩበት እንዲሆን እንዲሁም የሀገራችንን  ብልጽግና በአጠረ ጊዜ ዕውን ለማድረግ የምንነሳበት ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ ፤ የ"ጊፋታ" በዓል ባህላዊና ታሪካዊ ይዘት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

"ጊፋታ" ወደ አዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ መሻገርን የሚያሳይ በዓል በመሆኑ ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር በስራ፣ በንቃትና በታደሰ ስነልቦና እንዲቀበለው ጥሪ አቅርበዋል።

ጎረቤት ዘመድ አዝማድ እርስበርስ የሚገናኙበትና እንደየባህሉ ፍቅርን የሚቋደሱበት መሆኑ ለሰላም መጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ሰላምና አንድነት ለሁሉ ነገር መሰረት መሆናቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤  ባህላዊ እሴቶቻችን ለዚህ ቅድሚያ የሚሰጡት በመሆኑ ይህን በማጠናከር ለሀገርን ሰላምና አንድነት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።

በጊፋታ በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ በጊፋታ በዓልና ቋንቋ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍ በምሁራን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ሳምንቱን በተለያዩ ኩኔቶች ስከበር የቆየው የ"ጊፋታ" በዓል በተለያዩ መሰናዶዎች በድምቀት እየተከበረ   እስከነገ  እንደሚዘልቅ የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም