ጸደይ ባንክ ስራውን ጀመረ

335

መስከረም 14 ቀን 2015 (ኢዜአ)  ፀደይ ባንክ ቀልጣፋና ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓትን ለኀብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ለአገር ልማት የበኩሉን አሻራ ማሳረፍ እንዳለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም  በሚል ስያሜ  አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ፀደይ ባንክ ወደ ባንክነት አድጎ  ዛሬ በይፋ ስርውን ጀምሯል፡፡

በባንኩ ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ፣የአዲስ  አበባ ምክትል ከንቲባ  አቶ ጃንጥራር አባይና የብሔራዊ  ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተገኝተዋል፡፡  

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት ባንኩ "አብቁተ" በሚል ስያሜ  ባለፉት 26 ዓመታት በአማራ ክልል የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል ትልቅ የልማት መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል ብለዋል፡፡

በክልሉ የቁጠባ ባህል እንዲያድግም ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ባንኩ  ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት በማዘመንና ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ጋር በማጣመር አገልግሎት መስጠት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ባንኩ ለባለሃብቶችና አነስተኛ ቢዝነስ አንቀሳቃሾች ብድርን ጨምሮ ዘመናዊና ቀልጣፋ የፋይናንስ ስርዓት ተደራሽ በማድረግ ለአገር ልማት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተደደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፤ ባንኩ በቀጣይ ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋትና አገልግሎቱን ለማዘመን ለሚያከናውነው ተግባራት የክልሉ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያድርግ  አረጋግጠዋል፡፡

ባንኩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ ብቃት ያላቸው አመራሮችና በሥነ ምግባር የታነጹ ባለሙያዎች በማፍራት በዘርፉ ተመራጭ መሆን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ለበርካታ ዓመታት ያዳበረውን የማይክሮ ፋይናንስ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም እንዲሁ፡፡

የአብቁተ ወደ ፀደይ ባንክ ማደግ እንደ አገር የባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ሚናው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ናቸው፡፡

የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ባንኩ  የነበሩትን ደንበኞች በማቀፍ አዳዲስ ደንበኞችን እና አሠራሮችን በመጨመር የተጠናከረ የፋይናንስ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ባንኩ በአሁኑ ሰዓት 12 ሚሊዮን ደንበኞችና 500 ቅርንጫፎች እንዳሉትም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም