የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን ማጠናከርና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት መስጠት የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ ነው--አቶ ደስታ ሌዳሞ

123

ሐዋሳ (ኢዜአ) መስከረም 13/2014 የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን ማጠናከርና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የታዩ ክፍተቶችን ማረም ላይ ያተኮረ የሲዳማ ክልል የጤና ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።

በጉባኤው የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንደተናገሩት፣ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን ማጠናከር አጠቃላይ የጤና ሴክተሩን ሥራ የተሳለጠና የተሳካ ያደርገዋል።

እንደሃገር በአዲስ መልክ የተጀመረው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በ2014 በጀት በክልሉ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፣ "በዘርፉ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም ቀሪ ተግባራት አሉ" ብለዋል።

በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ ከሚከናወነው የመከላከል ሥራ በተጨማሪ የሕክምና አገልግሎቱን ማጠናከር እንደሚገባም አቶ ደስታ አመልክተዋል።

በመሆኑም በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን ማጠናከርና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የእናቶችን እና ህጻናት ሞት ለመቀነስ የተያዘውን ግብ እንደ አንድ ማሳኪያ መንገድ ሆኖ ያገለግላል።

እንደእሳቸው ገለጻ በሽታን አስቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሕሙማን ማድረስም ሌላኛው የክልሉ መንግስት ትኩረት ነው።

"ለዚህም የጤና ተቋማቱን በግብአትና በሰው ሃይል የማጠናከር፣ የጤና ተቋም ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎችም የማስፋትና የተጀመሩትን የማጠናቀቅ ሥራ ይሰራል" ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ህዝቡ የሚፈልገውንና ወቅቱ የሚጠይቀውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው፣ ጉባኤው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በቀዳሚነት አጀንዳ አድርጎ መወያየቱን ጠቁመዋል።

"ይህም በአተገባበር ሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን በማረም በሽታን ቀድሞ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የተሳካ ለማድረግ ያለመ ነው" ብለዋል።

ሃላፊዋ እንዳሉት ማሻሻያዎች የተደረገበት አዲሱ የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በክልሉ ተግባራዊ ቢደረግም በሚፈለገው ልክ ለውጥ አልተመዘገበም።

እንደሃላፊዋ ገለጻ፣ በመድረኩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በ2014 በጀት ዓመት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ አተገባበር ላይ የታዩ ክፍተቶችም ትኩረት ተደርጎ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ዶክተር ሰላማዊት እንዳሉት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስምሪት ችግር፣ በጤና ጣቢያና ጤና ኬላ ያለው ትስስር ክፍተት፣ የጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎቹ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት አለመስራትና ሌሎች ችግሮች በፕሮግራሙ ሂደት በክፍተት የታዩ ናቸው።

በመድረኩ በጤናው ዘርፍ ባከናወኑት ተግባር እውቅና ካገኙ ተቋማት መካከል የአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ሃንቄ፣ ሆስፒታሉ በ2014 በርካታ አዳዲስ የሕክምና አገልግሎቶች መጀመሩን ገልጸዋል።

ከአንገት በላይ ሕክምና፣ የዓይን፣ የሳይካትሪ፣ የቆዳና ሌሎች ሕክምናዎች በአዲስ መልክ መጀመራቸውን ጠቁመው፣ "የእውቅና ሽልማቱ በቀጣይ ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን እንድንጀምር መነሳሳት ይፈጥሯል" ብለዋል፡፡

የይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ሰርሚሶ በበኩላቸው ያገኙት የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት "ከዚህ ቀደም ለተሰራው ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ስራችን ስንቅ ነው" ብለዋል።

በጤና ተቋማት እየተተገበረ ባለው "ጥምረት ለጥራት" በሚለው አሰራር በአቅራቢያቸው የሚገኙ ሆስፒታሎችን በመደገፍ በሰሩት ሥራ ውጤት መመዝገቡንም አመልክተዋል።

በመድረኩ 20 የጤና ተቋማትና ሴክተሮች በተለያየ ዘርፍ ባስመዘገቡት የላቀ አፈጻጸም የገንዘብ፣ የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ሆነዋል።

ጉባኤው በ2014 በጀት ዕቅድ አፈጻጸምና በአዲሱ ዓመት ዕቅድ ላይ እያካሄደ ያለው ውይይት እስከ ነገ ቀጥሎ እንደሚውል ታውቋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም