ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት በውሸት የተሞላና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር ነው- ካናዳዊው የዓለም አቀፍ ወንጀል ሕጎች ባለሙያ

158

መስከረም 13 ቀን 2015(ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት በውሸት የተሞላና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር መሆኑን ካናዳዊው የዓለም አቀፍ የወንጀል ሕጎች ባለሙያ ጆን ፒሎት ተናገረ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገው የህግ ባለሙያው ጆን ፒሎት ሪፖርቱ ” የአገሪቱን ሉዓላዊነት ያላከበረ ሲሆን ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጥምር ያወጡትን ሪፖርት የተጻረረና በሪፖርቱ የወጡ ግኝቶችን ወደ ኋላ የገፋ ነው" ብሏል፡፡

ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያ ህዝቦችን በርሃብ ለመቅጣት ትሞክራለች በማለት በሐሰት ለመውቀስ የሞከረ ነው በማለት ሪፖርቱን አጣጥሎታል፡፡

"እኔ ያነበብኩት ማስረጃ በተቃራኒው ኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ምግብ ለማዳረስ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ ማድረጓን የሚያሳይ ነው ” ሲል ጆን ፒሎት ተናግሯል፡፡

የህግ ባለሙያው እንደሚያምነው ሪፖርቱ አስፈላጊ የተባሉ ማረጋገጫዎችን ያልያዘ ሲሆን በአንፃሩ የሚፈልጉትን መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው፡፡

የሰብዓዊ መበት ምርምራ ኮሚሽን ባለሙያዎች መጀመሪያ ሪፖርቱን ከፃፉ በኋላ ግኝቶችን በመፈለግ እውነት ለማስመሰል መሞከራቸውን አጋልጧል፡፡

አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ ወንጀሎችን መፈጸሙን፣ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙንና መዝረፉን በማስታወስ እነዚህ ሁሉ ወንጀሎች በማስረጃ የተረጋገጡ ቢሆንም በሪፖርቱ ላይ አልተካተቱም በማለት የታቀደውን ደባ አጋልጧል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ባለሙያው ሲያብራራ "ዋሽተዋል፣ የማይፈልጉትን ሃሳብ አስወግደዋል ወይም የፈለጉትን በመምረጥና በሚፈልጉት ቃላት በማሽሞንሞን ለማታለል ሞክረዋል" ነው ያለው፡፡

የኮሚሽኑ ፖለቲካዊ ዓላማ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት መጣሱን አንስቶ፤ በተዛባና በተሳሳተ መላምት የተዘጋጀው ሪፖርት ግብ ከዚህ ቀደም በጥምር ቡድኑ የወጣውን ሪፖርት ለማጣጣል ያለመ ነው ብሏል።

ጆን ፒሎት ሪፖርቱ በጣም ደካማና ዓለምአቀፍ ህጎችንና የአገሪቱን ሉዓላዊነት ያላከበረ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም