በክልሉ ቀሪ የመሬት እርጥበትን ተጠቅሞ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት እየተሰራ ነው

120

ባህር ዳር መስከረም 13/2015  (ኢዜአ)  በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት ከመመከት ጎን ለጎን ቀሪ የመሬት እርጥበትን ተጠቅሞ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤልያስ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቀሪ የመሬት እርጥበትን ተጠቅሞ 200 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ለእዚህም ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ዕቅዱ እንዲሳካ የሚያስችል ሙያዊ ድጋፍ ለአርሶ አደሩ ከመስጠት ጀምሮ ተገቢ ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

"አሸባሪው ህወሓት እያካሄደ ያለውን ጦርነት ከመመከት ጎን ለጎን አርሶ አደሩ ፈጥነው የደረሱ ገብስና ሌሎች ሰብሎችን በመሰብሰብና መሬቱን ደጋግሞ በማረስ ከመጭው ጥቅምት ወር ጀምሮ የዘር ሥራ ይጀመራል" ሲሉም አቶ ኤልያስ አመልክተዋል።

ባለሙያው እንዳሉት ቀሪ የመሬት እርጥበትን ተጠቅሞ ከሚለሙ ሰብሎች ገብስ፣ ቀይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽንብራ፣ ጓያ፣ ምስር፣ አብሽ፣ ድንች፣ ኑግ እና ቲማቲም ይጠቀሳሉ።

የክረምቱ ዝናብ የሚወጣበት ጊዜ የሚረዝም ከሆነ ለማልማት በዕቅድ የተያዘው የመሬት መጠን ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ባለሙያው አመልክተዋል።

በእዚህ የግብርና ልማት ከ796 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን ከሚያለሙት መሬትም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ቀሪ የመሬት እርጥበትን ተጠቅመው ከሚያለሙ አርሶ አደሮች መካከል በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የላታ ቀበሌ ነዋሪ አዘነ ዳኘ በክረምቱ ያለሙትን የበቆሎ ሰብል አንስተው ሽንኩርት ለማልማት ከወዲሁ የእርሻ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት ቀደም ሲል ጓያና ሽንብራ ሲዘሩ ያገኙት የነበረው ምርት ከ3 ኩንታል እንደማይበልጥ ነበር።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቀሪ የመሬት እርጥበት የጀመሩት የሽንኩርት ልማት ሥራ የተሻለ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

"ዘንድሮ ቀሪ እርጥበትን በመጠቀም ከማለማው ግማሽ ሄክታር መሬት እስከ 80 ኩንታል የሽንኩርት ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ እሆናለው" ሲሉም ገልጸዋል።

ያለሙትን በቆሎ እና ድንች ሰብስበው በመሬቱ ላይ ተጨማሪ ልማት ለማካሄድ የእርሻ ሥራ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የእዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር አያናው ጫኔ ናቸው።

ከግማሽ ሄክታር በላይ መሬታቸውን ከቀጣይ ጥቅምት ወር ጀምሮ በቲማቲም፣ ቃሪያ እና ሽንኩርት ለማልማት መሬታቸውን እያዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምቱ ዝናብ ዘግይቶ በመውጣቱ 300ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቀሪ እርጥበት ለምቶ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መቻሉን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም