ህብረተሰቡ ለመስቀል ደመራ በዓል የሚጠቀምባቸው ደመራና ችቦ የእሳት አደጋ እንዳይፈጥሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

162

መስከረም 13 /2015 (ኢዜአ)  ህብረተሰቡ የመስቀል ደመራ በዓል የሚጠቀምባቸው ደመራና ችቦ የእሳት አደጋ እንዳይፈጥሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳስቧል፡፡

ደመራ ሲደመር ከኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መስመሮች፣ ከነዳጅ ማደያዎች፣ ከጋራዦች እንዲሁም ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ከሚገኙባቸው ስፍራዎች መራቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች አንዷ አዲስ አበባ ናት።

የደመራ ስነስርዓቱም የፊታችን መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ  አበባ  መስቀል  አደባባይና ሌሎችም የመዲናዋ አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን በተገኙበት ይከናወናል።  

የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን  የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንዳሉት ኮሚሽኑ በመስቀል ደመራ በዓል ወቅት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እየሰራ ነው።

አቶ ንጋቱ በመጪው ሰኞ የአደጋ ጊዜ ቅነሳ ባለሙያዎች ደመራ የሚደመርባቸውን ቦታዎች የአደጋ ስጋት በመፈተሽ በየአካባቢው የቁጥጥር  ስራ ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ደመራው ሲደመር ከኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መስመሮች፣ ከነዳጅ ማደያዎች፣ ከጋራዦች እንዲሁም ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ከሚገኙባቸው ስፍራዎች መራቅ እንዳለበት አቅጣጫ እንደሚሰጡም ነው የተናገሩት።

የመዲናዋ ነዋሪዎችና አብያተ ክርስቲያናትም የመስቀል ደመራና ችቦ በሚለኩሱበት ወቅት የእሳት አደጋ እንዳይፈጠር ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ በዓሉ ያለምንም የእሳት  አደጋ እንዲከናወን በመዲናዋ በተመረጡ አካባቢዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠሩንም  ተናግረዋል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን ርችት እንዳይተኩሱ በመከልከል ራሳቸውን ከአደጋ ሊያርቁ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አደጋ ሲያጋጥም ህብረተሰቡ በኮሚሽኑ  በቀጥታ  የስልክ  መስመሮች 011 155 53 00 ወይም 011 156 86 01 እንዲሁም በነጻ የስልክ  መስመር  939 በመደወል ማሳወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም