በአገራችን የሚገኙ የገጸና የከርሰ ምድር ውሃ ሃብትን በማልማት ለአገራችን ብልፅግና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል

76

መስከረም 13 /2015 (ኢዜአ) በአገራችን የሚገኙ የገጸና የከርሰ ምድር ውሃ ሃብትን በማልማት ለአገሪቱ ብልፅግና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለፁ።

የውሃና ኢነርጀ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አስመልክቶ ከተጠሪ ተቋማትና ከክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች ጋር የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ያላትን የገጸና የከርሰ ምድር ውሃ በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው።

ባለፈው ዓመት በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ በተሰራው ጠንካራ ስራ ከ5 ሚሊየን በላይ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

ይህም አገራችን የአሸባሪው ህወሃት የከፈተውን ጦርነት ከመመከት ጎን ለጎን የተከናወነ ተግባር በመሆኑ አበረታች ውጤት የተገኘበት ዓመት ነበር ብለዋል።

በኢነርጂ ልማት ዘርፍም በግድብ ግንባታ፣በሶላር፣ በነፋስና ሌሎች ዘርፎች ሃይል በማመንጨት በተለይም የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ3ኛው ዙር የውሃ ሙሊትና የ2ኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት አገራችን የጀመረችውን የኢኮኖሚ ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የባለፈውን ዓመት ጥንካሬ በማስቀጠልና ድክመቶችን በማረም ከባለፈው ዓመት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም