ዩኤንዲፒ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሞክሮ ለ10 የአፍሪካ አገሮች ሊያጋራ ነው

106

መስከረም 13/ 2015 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሞክሮ ለ10 የአፍሪካ አገሮች ሊያጋራ ነው።

በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 77ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ዩኤንዲፒ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሞክሮ ላይ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

May be an image of 9 people and people standing

በመድረኩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ቀጣናዊ ትስስርን እንደሚያጠናክርና በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለተወሰኑ ጎረቤት አገሮች ችግኝ ማቅረቧን አስታውሰው፤ ቀጣናዊ ትብብሩን ለማጠናከርና የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመቋቋም ችግኝ የማቅረቡ ተግባር እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የማህበራዊ-ኢኮኖሚ ቀውስን ጫና እንደሚያቃልል ጠቅሰው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት እየተተገበረ ለሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዩኤንዲፒ ያለውን አጋርነት አድንቀዋል።

ዩኤንዲፒ ድጋፉንና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። መርሐ ግብሩን መደገፍ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ደመቀ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም፣ ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ፣ በረሃማነትን ለመከላከል፣ የአረንጓዴ ልማትን ለማረጋገጥ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኤንዲፒን በመወከል በመድረኩ የተገኙት አልሀጂ ፎል በበኩላቸው መርሐ ግብሩ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ልማት የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ ገልጸዋል። ዩኤንዲፒ የመርሐ ግብሩን ተሞክሮ በቀጣይ በ10 የአፍሪካ አገሮች እንደሚያጋራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም