ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተግባቦት ስራ እንዲጠናከር ተጠየቀ

85

መስከረም 12 /2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተግባቦት ስራ እንዲጠናከር የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠየቀ።

በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ በተዘጋጀው ስትራቴጂክ ረቂቅ እቅድ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ከምክክሩ በፊት፣ በምክክሩ ወቅት እንዲሁም ከምክክሩ በኋላ ግልጽ የተግባቦትና የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር አገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ማድረግ ይገባል ተብሏል።

የኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ስትራቴጂክ ረቂቅ እቅድ የተግባቦትና የመረጃ ልውውጥን በማሳለጥ ምክክሩ አካታችና ግልጽ እንዲሆን ለማገዝ የተዘጋጀ መሆኑ ተብራርቷል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፤ የረቂቁ አላማና ይዘት የመገናኛ ብዙሃን ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ለማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም አካታችና ግልጽ ምክክር ለማካሄድ የምክክርን ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ ጽንሰ ሃሳብ፣ አላማና አጠቃላይ ሂደቱን ለህዝብ ማስተማር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተግባቦት ስራ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ ለአገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ልየታ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች አገራዊ ምክከሩ እንዲሳካ ሁሉም በሙያቸው አስፈላጊውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ከሚዲያና ኮሚኒኬሽን ስትራቴጂ ረቂቅ ዕቅድ በተጨማሪ የኮሙኒኬሽን አጋርነትና ትብበር ሰነድ ቀርቦ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ተደርጎበታል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አለመግባባትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ለሚደረገው ጉዞ የውይይት ባህልን ማዳበር ከተቋቋመበት አላማ ውስጥ ይጠቀሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም