በኢትዮጵያ አነስተኛ የንግድ ስራዎችን በዲጂታል መሳሪያዎች ማቀላጠፍ የሚያስችል የ"ሜታ ቡስት" መርሐ ግብር ተጀመረ

140

መስከረም 12/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አነስተኛ የንግድ ስራዎችን በዲጂታል መሳሪያዎች ማቀላጠፍ የሚያስችል የ"ሜታ ቡስት" መርሐ ግብር በሜታ ኩባንያ ተጀመረ።

ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ የተሰኙ መተግበሪያዎችን የሚያንቀሳቅሰው የሜታ ግሩፕ ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እና ከሰመር ሚዲያ ጋር በመተባበር ዛሬ የ"ሜታ ቡስት" መርሃ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።

የመርሐ ግብሩ ግብ የጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ ቢዝነሶች ዲጂታል መሣሪያዎችን በመጠቀም በበይነ መረብ የንግድ ሥራቸውን ከማቀላጠፍ በተጨማሪ ለደንበኞቻቸው ተደራሽ እንዲሆኑ ዕድል መፍጠር ነው።

በ'ሜታ ቡስት' ፕሮግራም መሰረት በ2015 ዓ.ም በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ለ5 ሺህ የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ቢዝነሶች የበይነ መረብ ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ የወጣቶችና ሴቶች የስራ አጥነት ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።

መንግስት በዓመት ለ3 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሜታ ቡስት መርሐ ግብርም በተለይም ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅና ንግዳቸውን ይበልጥ ለማሳለጥም ያግዛል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ፌስቡክን ጨምሮ የማህበራዊ ሚደያ መተግበሪያዎች ከአፍራሽ ተልዕኮ ማሰራጫነትና ከጊዜ ብክነት ባሻገር ለምጣኔ ሀብታዊ ግልጋሎት በማዋል ገንቢ ተጽዕኖ እንዲፈጥሩም ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

በኢኖሼንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ባዩ በ2015 ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ከሚተገበሩ ስራዎች መካከል በዕለቱ ይፋ የተደረገው ፕሪግራም አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

በምሥራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ የሜታ የሕዝብ ፖሊሲ ዳይሬክተር ሚርሲ ንዴጓ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን በመደገፍ ለኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።

በእስካሁኑ ሙከራዎች አበረታች ወጤቶች እንደነበሩ አወስትው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆን የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ምሰሶ የሆኑ አነስተኛ የንግድ ተቋማትን የዲጂታል ግብይት ክህሎት እንዲያሟሉ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ሜታ በፌስቡክን ጨምሮ በኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ በሚፈጥሩ በርካታ መተግበሪያዎቹ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት አነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ ሥራዎችን ሲደግፍ መቆየቱን አስታውስዋል።

ፕሮግራሙ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በሰመር ሚዲያ በኩል በኢትዮጵያ ሙከራ ባከናወናቸው ስልጠናዎች 7 ሺህ አነስተኛና መካከለኛ ቢዝነሶች ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም