የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማጣራት የተቋቋመው ቡድን ራሱን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ሊያርቅ ይገባል- የሰሜን ኮሪያ፣ ኪዩባና ቤላሩስ አምባሳደሮች

137

መስከረም 12/2015 /ኢዜአ/ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማጣራት የተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን ራሱን ከፖለቲካ ወገንተኝነት በማራቅ አላማው ላይ ብቻ ሊያተኩር ይገባል ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰሜን ኮሪያና የኪዩባና ቤላሩስ አምባሳደሮች ተናገሩ።

በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ስም በሃገራት የውስጥ ጉዳይ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶችና የተዛቡ አመለካከቶች ሊስተካከሉ ይገባል ያሉት አምባሳደሮቹ ፖለቲካዊ እሳቤያቸው የጎላና የተዛቡት አካሄዶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል በማለት አስጠንቅቀዋል።

ሂደቶቹ በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ ለንግግርና ሰላማዊ አማራጭ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ያከብዱታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለችግሮቿ የራሷን መፍትሄ እንድትፈልግ ድጋፍ እናደርጋለን ያሉት አምባሳደሮቹ የጉዳዩ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ያልተስማማችባቸውን ውሳኔዎች ማሳለፍ ሃገሪቱን ከመረበሽ በዘለለ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት መዳፈር መሆኑን አንስተዋል።

የምርመራ ኮሚሽኑ የተቋቋማበትን አላማ ብቻ አሳክቶ ስራውን በዚሁ ሊያጠናቅቅ ይገባል ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ተፈጽሟል የተባለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለመመርመር የተመሰረተው ኮሚሽን ያቀረባቸውን ሃሳቦች ኩባ እንደማትቀበላቸውም አምባሳደሩ ግልጽ አድርገዋል።

ኩባ ታዳጊ ሃገራት ያሉባቸውን ችግሮች በራሳቸው እንዲፈቱ ሁኔታዎች ሊመቻችላቸው ሲገባ በዚህ ምክር ቤት የሚነሱ ሃሳቦች ሊጫኑባቸው እንደማይገባ በጽኑ ታምናለች ብለዋል።

ተደረገ የተባለው ምርመራም በድርብ ሚዛን /double standard/ የተሞላ ለአንድ ወገን ያጋደለ እንዲሁም ኢትዮጵያን የመጫን ፖለቲካዊ ፍላጎት ጎልቶ የታየበት መሆኑን አምባሳደሩ አንስተዋል።

ግጭቶችን በንግግር ለመፍታት የተቀረጹት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርሆዎች ከመድልዎና ከጫናዎች ነጻ መሆንን እንደሚያመለክቱ ያስታወሱት አምባሳደሩ ለሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶች መከበር እነዚህ መርሆዎች መጣስ እንደሌለባቸው አስረድተዋል።

ቤላሩስ በበኩሏ ኮሚሽኑ ከምስረታው ጀምሮ ፖለቲካዊ አላማ የነበረው ነው ብላለች።

ኮሚሽኑ ከተፈቀደለት ገደብ በላይ አልፎ በመሄድ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የተዳፈረ በመሆኑ የስራ ጊዜውን ማራዘሙ አያሳምንም ስትልም ተቃውማለች።

51ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባውን ከመስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ምክር ቤቱ ዛሬ በ11ኛ ቀን ውሎው በኢትዮጵያ ላይ ላይ አሳታፊ ውይይት (Interactive Dialogue) እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም