በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ800 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

135

ሰቆጣ  መስከረም 12/2015 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑና ለዘማች ቤተሰብ ተማሪዎች ከ800 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

የዞኑ የሴቶችና ህጻናት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ደመቅ አበባው ድጋፉ ከዞኑ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና የመንግስት ተቋማት የተሰባሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ግምታቸው ከ800ሺህ ብር በላይ የሆነ "ከ1ሺህ 200 በላይ ደርዘን ደብተር፣ 100 ፓኮ እስክርቢቶና ሌሎች የመማሪያ ግብአቶችን በማሰባሰብ ለተማሪዎች መከፋፈሉን አስረድተዋል።

"በድጋፉ ከ1ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ የቤተሰቦቻቸውን ጫና መቀነስ ተችሏል" ሲሉም ገልጸዋል።

ድጋፉ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ለማስቀረት ጠቀሜታ እንዳለውም ወይዘሮ ደመቅ አስረድተዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡን በማስተባበር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።

በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዳሉና በገንዳውሃ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ካባነሽ ስለሽ፣ ለሁለት ልጆቻቸው ደብተር እና እስክርቢቶ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ካለው የኑሮ ውድነት የተነሳ ለልጆቻቸው የመማሪያ ቁሳቁስ ለማሟላት ከብዷቸው እንደነበር ገልጸው፣ የተደረገላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ከጭንቀት እንደታደጋቸው ተናግረዋል።

ሌላዋ ድጋፍ የተደረገላት የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ ኢየሩሳሌም አድማሱ በበኩሏ፣ ወላጅ አባቷ አሸባሪውን ህወሓት ለመፋለም ወደግንባር በመሄዱ እናቷ ደብተርና እስክሪቢቶ ለማሟላት ተቸግራ እንደነበር ገልጻለች።

"ጓደኞቼ ደብተርና እስክብሪቶ ገዝተው ለትምህርት ሲዘጋጁ እኔ ከፍቶኝ ነበር" ያለችው ተማሪዋ፣ ዛሬ በተደረገላት የደብተር እና እስክርቢቶ ድጋፍ መደሰቷን ገልፃለች።

በቀጣይም በትምህርቷ በርትታና ጠንክራ በመስራት ላስተማራት ቤተሰብና እና ለቤተሰቦቿ ኩራት ለመሆን ጠንክራ እንደምትማር ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም