የመስቀል ደመራ በዓል በሀዋሳ በሠላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ

232

ሀዋሳ ፤ መስከረም 12/2015 (ኢዜአ) ፡- በሀዋሳ የመስቀል ደመራ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሠላም እንዲከበር በተቀናጀ መልኩ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ። 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረስብከት በበከሉ፤ የመስቀል ደመራ በዓል ሀይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቁ መልኩ በድምቀት ለማክበር የዝግጅት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡

ሀዋሳ የቱሪስት መዳረሻ ከመሆኗም ባሻገር ሐይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በድምቀት የሚከበሩባት ከተማ መሆኗን የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ ለኢዜአ ተናግረዋል ፡፡

በከተማዋ የመስቀል ደመራ በዓል በተለመደው ድምቀት ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር ፖሊስ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ነው ያስታወቁት ፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በአደባባይ የሚከበርና በርካታ ህዝብ የሚሳተፍበት  በመሆኑ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ለማድረስና ከተማዋን ለማወክ የሚሞክሩ አካላትን ለመቆጣጠር  በማሰብ ማህበረሰብ አቀፍ የግንዛቤና የጥንቃቄ ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የከተማዋ ፖለስ ከሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የፀጥታ የጋራ ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል ፡፡

ከተማዋ አሁን ያላት ሠላማዊ ገፅታ የህዝቡ ሠላም ወዳድነት እንዲሁም እኛም ከህዝቡ ጋር ተናበን የመስራታችን ውጤት ነው ብለዋል ፡፡

በክፍለ ከተማ፣ በቀበሌና በመንደር ደረጃ ካሉ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረዋል ፡፡

ከሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም ከቤት አከራዮች ጋር የጠበቀ ቁርኝት በመፍጠር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥና የፀጥታ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል ፡፡

ከቤተክርስቲያኒቱ ወጣቶችና አባቶች ጋርም በዕለቱ በሚኖሩ የፍተሻና የፀጥታ አጠባበቅ ሥራ ላይ በጋራ  እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል ፡፡

በዕለቱ የደመራ በዓል ከሚከበርበት መስቀል አደባባይ አቅራቢያ ዳኛ፣ ዐቃቤ ሕግና መርማሪ ፖሊስ የተካተቱበት ጊዜያዊ ምድብ ችሎት እንደሚቋቋምም ነው ያስረዱት ፡፡

አንዳንድ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች በዕለቱ የሚፈጠረውን የተሳፋሪ ብዛት እንደአጋጣሚ ተጠቅመው ታሪፍ በመጨመር ህብረተሰቡን ለእንግልት እንዳይዳርጉ ከማስገንዘብ ባለፈ የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚደረግ አመልክተዋል ፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎችም ሆኑ ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች የፀጥታ አካላትን እገዛ ለማግኘትና ጥቆማ ለመስጠት በ 046 220 1046 እንዲሁም 091 658 6115 መደወል እንደሚችሉም  ኮማንደር ደረሰ አስታውቀዋል፡፡

በዕለቱ በጊዜያዊነት ለተሸከርካሪዎች ዝግ የሚደረጉ መንገዶች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ መጋቤ አዕላፍ ኃይለፅዮን አባዲ ፤የመስቀል ደመራ በዓል የኢትዮጵያዊያን የማንነታቸው መገለጫ ቅርስ ከመሆኑም ባሻገር የክርስቶስ ፍቅርና ፍፁም ሠላም የሚንፀባረቅበት የአደባባይ በዓል ነው ብለዋል ፡፡

የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓትና ትውፊት በጠበቀ መልኩ እንደወትሮው ደምቆና ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር የበዓል አከባበር ዐብይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማዋቀር በቂ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት ፡፡

ከከተማዋ አስተዳደር  ፖሊስና የአስተዳደር አካላት ጋርም በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል ፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ በዕለቱ የመስቀሉን ፍቅር እና ኢትዮጵያዊ የአብሮነት እሴቱን በሚያሳይ ድምቀት እንዲያከብርም በየአጥቢያው መልዕክት መተላለፉን ጠቁመዋል ፡፡

በሀዋሳ ከወርሀ ነሀሴ 2014ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የመስቀል ደመራ በዓል ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ በሀገረስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ መጋቤ ልዑካን አንዳርጋቸው ሙሉጌታ ናቸው።

በከተማው ካሉ ከሁሉም አጥቢያ የተውጣጡ ከ250 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በኮሚቴ ተደራጅተው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል ፡፡

ወጣቶቹ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት በመግቢያ በሮች በሚደረጉ ፍተሻዎችና በሥርዓት ማስከበር ላይ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ ብለዋል ፡፡

ከየአጥቢያው ወደ መስቀል አደባባይ በሚደረገው ጉዞ በካህናትና በሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚከወኑ ሥርዐቶች፣ ዝማሬዎችና በባነር የሚተላለፉ መልዕክቶች የመስቀሉን ፍቅር፣ የደመራ በዓልን መሰረታዊ አመጣጥ የሚያሳዩ እንዲሆኑ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በመስቀል አደባባይ በሚኖረው መርሀግብርም ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት፣ ትርዒት እንዲሁም ያሬዳዊ ጥዑመ ዜማዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም