ዛሬም ነገም ለአገር ክብርና ሉዓላዊነት መከበር ከቆመው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ነን

205

ነቀምቴ፣ ጭሮ፣ ጅማ፣ ሻሸመኔ መስከረም 12/2015 (ኢዜአ) ''ዛሬም ነገም ለአገር ክብርና ሉዓላዊነት መከበር መስዋዕትነት አየከፈለ ከሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ነን'' ሰሉ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት የዘመናት ታሪኩ የሚያስረዳው ከራሱ አገርና ሕዝብ አልፎ ለሌሎች የተረፈ ነው።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ሰላም በጠፋበት በተለያዩ አገራት ሰላም አስከበሮ የአገሩንም ሰንደቅ አላማ ከፍ ያደረገ የአገር ኩራት ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በተለያየ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የሚኖሩ አስትያየት ሰጪዎች ሰራዊቱ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም የአገር ኩራትና ክብር ነው ይላሉ።

የነቀምቴ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ናስር ኑሩ እንዳሉት ሰራዊቱ ለአገሩ ክብርና ሉዓላዊነት መከበር ቤቱንና ቤተሰቡን ሳይል ውድ ሕይወቱን እየሰዋ ይገኛል።

ሁሉም ሰው በሰላም ወጥቶ የሚገባው፣ ንግዶ የሚኖረው፣ የአገር ዳር ድንበር የተከበረው በሰራዊቱ መኖር ነው ብለዋል።

እሳቸውም ባሳለፉት እድሜያቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአገሩ ክብር ሲከፍል የኖረውን መሰዋዕትነት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

አባ ገዳ ጅሬኛ ገመዳ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሕዝቡ የወጣና ለሕዝብና ለአገር ክብር የቆመ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰራዊቱ የማይበገር የሕዝብ ልጅ በመሆኑ ክብር የሚገባውና ሕዝቡ ከጎኑ በመቆም የኋላ ደጀን ሊሆንለት ይገባል ነው ያሉት።

የአገር ሽማግሌው አቶ ታደሰ ኡርጌሣም እንዲሁ ''የአገር መከላከያ ሠራዊት ማለት ለአገሪቱ የሕግ የበላይነት መከበር የቆመ፤ ከሕዝቡ የወጣ ለህዝቡና ለአገር ዳር ድንበር መከበር የቆመ ኃይል ነው'' ብለዋል።

ሰራዊቱ ለዘመናት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአከባቢና በሌሎች ምክንያት ሳይከፈል የአገር ጠባቂነትን በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን በኦዳ ቡልቱም ወረዳ ነዋሪው አቶ ቀናቴ አበበ ''መከላከያ ሰራዊታችን የአገራችንና የህዝቦቿ ሉዓላዊነት ጠባቂ ነው'' ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ መካለከያ ሰራዊት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ የኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እየጠበቀ ዘመናትን አሳልፏል ብለዋል።

የጭሮ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዘነብ ጥላሁን ''ሰላም ለልጆቻን፤ ለጎረቤቶቻችን ለኢትዮጵያችን ያስፈልገናል፤ ሰራዊቱ ደግሞ ይህ እንዲኖር ነው ዋጋ የሚከፍለው'' ሲሉ ተናግረዋል።

ሰራዊቱ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት እንዲኖር፤ በወንድማማችነት እንዲተሳሰብ ለማድረግ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ የሚዋደቅ መሆኑንም አንስተዋል።

ወይዘሮ ወይንሸት አበራ በበኩላቸው ''አልበገር ባዩ መከላከያ ሰራዊታችን ባይኖር እኛ ዛሬ እንደ ሶሪያዊያንና እንደ ሌሎች አገራት እንሆን ነበር'' በማለት የሰራዊቱን ዘመን ተሻጋሪ ጥንካሬ ያነሳሉ።

''ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እራሱን ሰውቶ ኢትዮጵያን ለማዳን የቆረጠ ነው'' የሚሉት ደግሞ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

በአስቸጋሪ መልክዓምድር ጭምር ቀን ከለሊት ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር የሚተናነቀው ጀግናው ሰራዊታችን ለሀገራችን ሰላምና ነጻነት አለኝታ መሆኑን እንረዳለን የሚሉት ኢኒስፔክተር ፈይሰል ጀበል ሰለ ጀግናው ሰራዊታችን ሲገልጹ ሰራዊቱ የኢትዮጵያውያን መከታ ነው ብለዋል።

ሀገር ነጻነቷ እንዲከበር፤ የዜጎቿ ደህንነት እንዲጠበቅ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸው ''እኛም ከሰራዊቱ ጎን ቆመን ለመታገል ዝግጁ ነን'' ብለዋል።

የጅማ ዞን የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጁነዲን ይማም መከላከያ ሰራዊት ህልውናችን በመሆኑ በሁሉም ነገር ልንደግፈውና አብረነው ልንቆም የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰላማችንና የነጻነታችን ዋስትና መሆኑን ተረድተን በሞራል፣ በገንዘብ እንዲሁም ግንባር በመዝመት ጭምር ለመሳተፍ ዝግጁ ነን ብለዋል።

የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ አቶ ቡሹራ አመዮ እንዳሉት መከላኪያ ስራዊት ቀን ከለሊት ደከመኝ  ስለችኝ ሳይል ለሀገሩ ክብር የቆመ ጀግና ነው ብለዋል።

''ሀገር ማለት ስው ነው፣ እኔ እና የሀገራችን ህዝቦች በጠላት እንዳንወረር ከጠላት ጋር ፊት ለፊት እየተፍለመ ለሚገኙው  ለመከላኪያ ስራዊታችን ከብርና ምስጋና አለኝ'' ሲሉም ይገልጻሉ።

ሌላው ከተማ ነዋሪ ወይዝሮ ወይኒቱ በየነ በበኩላቹው፣ መከላከያ ስራዊት ኢትዮጵያ ክብሯ ተጠብቆ ያስቀጠለና ሊከበር የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።

መከላኪያ  ስራዊት ለየትኛውም አካል የፖለቲካ ውግንና የሌለውና ለሀገሩ ሉዓላዊት ብቻ የቆመው  ጀግና ሰራዊት ነው ሲሉ ገልጸዋል ።

አስትያየት ሰጪዎች በምንም መልኩ ቢሆን ከአገር መከላከያ ሰራዊት እንደማይለዩና ድጋፋቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም