አገርን በብዝኃ ማንነት እሴት በመገንባት ሂደት የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ነው

112

መስከረም 12 /2015 (ኢዜአ) አገርን በብዝኃ ማንነት እሴት መገንባት ሂደት ውስጥ የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

"ኑ የጋራ ቤታችንን እንገባ" በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የወጣቶች የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባባሪያ ማዕከል በጋራ ነው ያዘጋጁት።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልመሃዲ፤ የብዛኃ ማንነት ባህልና አገር በቀል እውቀት እንዲጎለብት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የጋራ ቤታችንን በጋራ የመገንባት ሂደት ላይ ያጋጠሙ ወቅታዊ ችግሮችን ለማለፍ ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባውም ተናግረዋል።

ወጣቶች በአገራቸው ላይ ረጅም ዕድሜ የሚኖሩባት በመሆኑ የአገራቸውን ሉአላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ የጋራ አቋም መያዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ወጣቶች የጋራ ቤታቸው በትክክለኛው መንገድ እንዲገነባ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

ብዝኃ ማንነት ያለን ህዝብ ብንሆንም በአድዋ በካራማራና በሌሎች ግንባሮች አባቶች ተዋድቀው ነጻነታችንን ያስከበሩ መሆኑንጠቅሰው አሁን ደግሞ በታላቁ የህዳሴ ግድብ በዚሁ እሴት መሰረትም ለወጣቱ ተስፋ የሚሆን ታሪካዊ ፕሮጀክት እያሳካን እንገኛለን ነው ያሉት።

መሰል ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ የአገር መገንባት ሂደቱን የተሳካ ማድረግ ከወጣቱ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ታላላቆችም ወጣቱን በብልሃት እና በብልጠት በመምራት ለአገር ግንባታ ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖርቲዎች የወጣቶች ተወካዮችና የወጣቶች ማህበራት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም