በሀገሪቱ ከ20 ሺህ በላይ አዲስ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል-ጤና ሚኒስቴር

193

ሀዋሳ መስከረም 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ20 ሺህ በላይ አዲስ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በህብረተሰቡ  ዘንድ እየታየ ባለው መዘናጋት የኤች አይ ቪ እና ኮቪድ 19 ስርጭት እንዳይስፋፋ በተለይም የሀይማኖት አባቶች  የግንዛቤ ማስጨበጥ ሰራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።

ጤና ሚኒስቴር በኮቪድ 19 ዙሪያ  ከኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤና ከሀይማኖት አባቶች ጋር የመከረበት መድረክ በሀዋሳ ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ  በወቅቱ እንዳሉት በወባ፣ ኤች አይቪ ኤድስና በኮሮና ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።    

በኤች አይቪ ኤድስ ዙሪያ በተስተዋለ መዘናጋት አሁንም በርካታ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው 2014 በጀት አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ  ከ20 ሺህ በላይ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ መላው ህዝብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበው “የሀይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን በማስተማር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በትኩረት መስራት አለባቸው” ብለዋል።

በተመሳሳይ በኮቪድ 19- ዙሪያ በህብረተሰቡ ውስጥ እየታየ ባለው መዘናጋት ቫይረሱ በሰዎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ግንዛቤ በማስጨበጥ ዙሪያ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳባቸው አስገንዝዋል።

የጤና ሚኒስትሯ አማካሪ ዶክተር ሙሉቀን ዮሀንስ በበኩላቸው በኮቪድ 19ም ሆነ በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት ይስተዋላል።

“በኮቪድ ዙሪያ የሚስተዋለው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የአለታ ወንዶ ቡርሳ ኦትልቾ ወረዳዎች ቤተክርስትያን ስራ አስኪያጅ መላከ ጽዮን ቀሲስ ድንቃለም እሸቴ እንዳሉት በኤች አይ ቪ ኤድስና በኮሮና ቫይረስ ማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዳለው ቢታወቅም ጥንቃቄ ላይ ክፍተት አለ።

ቤተክርስትያኗ በትዳር መወሰንና ከጋብቻ በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ እንደማይገባ በማስተማር ተከታዮቿን ከኤች አይ ቪ ኤድስ እንዲቆጠቡ ስታስተምር መቆየቷን አስታውሰዋል።

ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖችም ቢሆኑ መድሀኒቱን በአግባቡ መውሰድ እንዳለባቸው በማስተማር ረገድም የበኩሏን አስተዋጾ ስትወጣ መቆየቷን አውስተዋል።

ሆኖም ግን በሽታው እየጠፋ ነው የሚል እሳቤ እየተፈጠረ በመሆኑ መዘናጋት መኖሩን ጠቁመው ይህን መዘናጋት ለማስቀረት በቤተ ክርስትያኗ ስር የማስተማርና ግንዛቤ የማጎልበት ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

ህዝቡ ከጤና ባለሙያዎች በሽታው ስለ መጥፋቱ በይፋ እስካልተነገረው ድረስ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም