የምዕራብ ጎጃም ዞን ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ከ25 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

139

እንጅባራ ፤ መስከረም 12/2015(ኢዜአ)፡- የምዕራብ ጎጃም ዞን የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን ለመመከት በግንባር ለተሰለፈው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ25 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ መልካሙ ተሾመ ፤  አሸባሪው ህውሃት ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት የከፈተው ከልማት ስራዎቻችን ለመነጠል አልሞ ቢሆንም ልማቱን በማስቀጠል ፤ ጦርነቱን መመከት ግዴታችን ነው ብለዋል።

የሃገር ሉአላዊነት ማስከበርና ልማት የማይነጣጠሉ ገጽታዎች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ መልካሙ፤ዞኑ ለሰራዊቱ ድጋፍ እንዲውል ህዝቡንና ባለሃብቱን በማስተባበር ከ25 ሚሊየን ብር በላይ መገኘቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከዚህ ገንዘብ   ወስጥ  16 ሚሊዮን ብር የሚሆን የደረቅ ሬሽንና የእርድ እንስሳት ግንባር ለመላክ መዘጋጀቱና  ቀሪው ቀደሞ ተልኳል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ለዘላቂ ልማትና ዕድገት አስተማማኝ ዋስትና የሆነውን ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመደገፍ ህዝቡ የጀመረውን የደጀንነት ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል ዋና አስተዳዳሪው ።

በዞኑ የፍኖተ ሠላም ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ ፀሃይነሽ ዋሲሁን በሰጡት አስተያየት፤ በሀገራችን ሠርተን በሠላም እንዳንኖር ተደጋጋሚ ጦርነት የከፈተብንን አሸባሪ እየመከተ ላለው ሠራዊት የምንቆጥበው ነገር የለም ብለዋል።

የውጭ ጠላቶቻችን ፈረስ የሆነው አሸባሪው የህወሃት ቡድን  ያወጀውን ጦርነት በድል ለመወጣት ሰራዊቱን በመደገፍ  የደጀንነት ሚናችን በስንቅ ዝግጅትና በገንዘብ ድጋፍ መወጣት አለብን ሲሉ ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በግንባር ለተሰለፈው የመከላከያ ሰራዊት  የደጀንነት ሚናቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ  ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በላይ አክሊሉ ናቸው።

ለሰራዊቱ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪም ከሌላው ነዋሪ ጋር በመሆን ለዘማች ቤተሰቦች የትምህርት ቁሳቁስ፣ የቤት ኪራይና የበዓል መዋያ ገንዘብ በማበርከት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም