አሸባሪው ህወሃት የተቃርኖ ሃሳብ የሚያራምድን ሁሉ ማጥፋት ከምስረታው ጀምሮ የሚከተለው ስልት ነው - የትዴፓ ሊቀመንበር

166

መስከረም 11/2015 /ኢዜአ/አሸባሪው ህወሃት የተቃርኖ ሃሳብ የሚያራምድን ሁሉ ማጥፋት ከምስረታው ጀምሮ የሚከተለው ስልት ነው ሲሉ የትግራይ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናገሩ።

አሸባሪው ሕወሃት ከምስረታው ጀምሮ በአሻጥር ሲሰራ የኖረ ቡድን እንጂ ለሰላምና አብሮነት ደንታ የማይሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የትዴፓ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪው ህወሃት ከጥንት እስካሁን ለራሱ ጥቅም ብቻ እየሰራ ህዝብን በማሰቃየት ቀጥሎበታል ብለዋል።

የህዝብን ችግርና ስቃይ ለራሱ መጠቀሚያነት በማዋል በጦርነት ሁሌም ዓላማየን አሳካለሁ ብሎ የሚያምን የጥፋት ስብስብ መሆኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በቅርቡ ያዘጋጀውና አፈትልኮ የወጣው የጥፋት ሰነዱ ''ነፃነታችን በክንዳችን'' በሚል ባሰፈረው ጽንሰ ሐሳብም አሁንም ሕዝብን ለጦርነትና ለእልቂት ለመማገድ የሚሰራ መሆኑን ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።

በህወሃት የትግል ዘመን በማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሰብአዊ መብት ዙሪያ የተለየ ጥያቄ ማንሳት በጠላትነት ያስፈርጅ እንደነበር አስታውሰው ለዚህ በርካታ ማሳያዎች ነበሩ ብለዋል።

በትግል ወቅት ለእውነት ቆመው ይታገሉ የነበሩ በርካታ ጓዶች በአደባባይ የተረሸኑና ሚስጢራዊ ግድያ የተፈፀመባቸው እንዳሉ አስታውሰዋል።

በመሆኑም አሸባሪው ህወሃት የተቃርኖ ሃሳብ የሚያራምድን ሁሉ ማጥፋት ከምስረታው ጀምሮ የሚከተለው የፖለቲካ ስልት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ከህወሃት የትጥቅ ትግል መስራቾች መካከል አንዱ የነበሩት ዶክተር አረጋዊ በዴሞክራሲ፣ በድርድርና  በሰላም የማያምን የጨካኞች ስብስብ በመበራከቱ አሳቸውና ሌሎች ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ታጋዮች ድርጅቱን ቀደም ብለው ለመልቀቅ መገደዳቸውን አስታውሰዋል።

ድርጅቱ ኢትዮጵያን የማስተዳደር እድሉን ባገኘባቸው ዓመታት የዘረፋና የአፈና ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠሉ በህዝብ ግፊት ከስልጣን መወገዱንም ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ህወሃት በጥፋት አብረውት ሚራመዱ፣ ዓላማውን ከሚደግፉለትና በዘረፋ ሰንሰለት አብረውት ከሚሰሩ አካላት በስተቀር ለህዝብ ጥቅምና ለልማት መስራት የማይሻ ጥቅመኛ ቡድን መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ይህንን ቡድን ለአንደና ለመሸረሻ ጊዜ ከላዩ ላይ እንድወርድለት መታገል አለበት ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ።

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ሰላም ከሰፈነ ለበርካታ ዓመታት በፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ስለሚያውቅ በጦርነት፣ ሁከትና ትርምስ እድሜውን ለማራዘም እየጣረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑን የጦርነት አባዜና ሀገር የማፍረስ እቅድ በጋራ ሆነን ልንመክት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም