በስፖርት ከፍተኛ ችግር እየሆነ የመጣውን አበረታች መድሃኒት በመከላከል ሂደት የኢትዮጵያ ጠንካራ ስራ ተደነቀ

205

መስከረም 10/2015/ኢዜአ/ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርት ከፍተኛ ችግር እየሆነ የመጣውን አበረታች መድሀኒት በመከላከል ሂደት የኢትዮጵያ ጠንካራ ስራ የዓለም አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት አደነቀ።

አራተኛው የኢትዮጵያ የፀረ- አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የዓለም አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒትን ወክለው በዙም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ቶማስ ካፕዴቬሌ፤ ኢትዮጵያ በተለይም አትሌቲክስ በዓለም ትልቅ ስፍራ ካላቸው አገራት ተርታ መሆኗን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርት ከፍተኛ ችግር እየሆነ የመጣውን አበረታች መድሀኒት በመከላከል ሂደት የኢትዮጵያ ጠንካራ ስራ የሚደነቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህ ዙሪያ ድርጅታቸው የኢትዮጵያን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ለተሻለ ስራ እንድትዘጋጅ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል፤ ከአትሌቶች  ምርመራ ጎን ለጎን አበረታች ቅመሞችን አስመልክቶ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ይሕም ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ለአትሌቶች በዘርፉ  ለሚደረገው ምርመራ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት በሀገር ውስጥ የምርመራ ላብራቶሪ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵ ፀረ አበረታች ቅመሞች የባለስልጣኑ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ፤ በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት በፊት አበረታች መድኃኒት እንደ ሀገር ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ግን ችግሩ መቃለሉን ነው ያስረዱት።

በጉባኤው የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሃላፊዎች፣ የስፖርት ማህበራት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም