አሸባሪው ህወሓት የምርት ጊዜን ጠብቆ የሚያነሳው ተደጋጋሚ ጦርነት ሀገር በማዳከም ለጠላት አጋልጦ የሚሰጥ የኢኮኖሚ አሻጥር ነው

93

መስከረም 10/2015/ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሓት የምርት ጊዜን ጠብቆ የሚያነሳው ተደጋጋሚ ጦርነት ሀገር በማዳከም ለጠላት አጋልጦ የሚሰጥ የኢኮኖሚ አሻጥር መሆኑ ተገለጸ፡፡

አሸባሪው ህወሓት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸመው ንጹሃንን በመጨፍጨፍና ንብረት በማውደም ነው፡፡

በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በገባበት ወቅትም ንጹሃንን በጅምላ ከመረሸን ባለፈ ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ግለሰቦችን ንብረት በመዝረፍና በማውደም የሀገር ጠላት መሆኑን በአደባባይ አሳይቷል።

የሰሜ ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከኋላ በመውጋት የሀገር ክህደት ወንጀል ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሶስተኛ ዙር ድረስ ወረራ የሚፈጽመው አርሶ አደሩ ለምርት በሚዘጋጅበት ወቅት ነው፡፡

አሸባሪው ህወሓት "የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ" በሚል ባዘጋጀው ምስጢራዊ ሰነድ መንግስት በችግር ውስጥም ሆኖ ያሳካውን የእርሻ ስራና የኢኮኖሚ ልዕልና በማደናቀፍ ኪሳራ ማድረስ እንደሚገባ ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ በሰፈነው አንፃራዊ ሰላም የተጀመረውን የእርሻ ስራ የስንዴ ምርትና ሌሎች የኢኮኖሚ ስራዎች በማደናቀፍ እረፍት በመንሳት መንግስት የልማት ስራውን በመተው በእሳት ማጥፋት ላይ እንዲጠመድ ለማድረግ መዘጋጀቱን በሰነዱ ተገልጿል፡፡

በተለይ የአማራ ክልል አርሶ አደር ፊቱን ወደ ልማት በማዞሩ መንግስት ለሰላም ጥሪ በተዘናጋበት ወቅት ወረራ በመፈጸም ምርቱን ወደ ቤቱ እንዳያስገባ የማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚከስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አቡሌ መሀሪ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአማራና አፋር ክልሎች ጦርነት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ብቻ ከሶስት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት ሳይሰበሰብ ቀርቷል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው ጦርነት የምርት ጊዜን እየጠበቀ የሚያገረሽ በመሆኑ በግብርና ምርት እድገት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ 30 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ ጦርነቱ በምርት ወቅት ማገርሸቱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ ይጎዳዋል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም የከተማው ነዋሪ በመንግስት ላይ ለተቃውሞ እንዲወጣ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው በሰነዱ ገልጿል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የምርት ወቅትን ጠብቆ በአሸባሪው ህወሃት የሚቀሰቀሰው "የኢኮኖሚ አሻጥር ለመፍጠር ታስቦ ሊሆን ይችላል" ያሉት ዶክተር አቡሌ፤ በክረምት ዝናብ እርሻ ላይ ለተመሰረተው የኢትዮጵያ አርሶ አደር አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ማምረት ካልቻሉ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት የመንግስትን እርዳታ ለመጠበቅ ይገደዳሉ ነው ያሉት።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የግብርና ምርት እንዲቀንስ በማድረግ በሰብዓዊ በዕርዳታ ሰበብ የምዕራባውያን ተላላኪ እንድትሆን የታሰበ አሻጥር ሊሆን ይችላልም ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት አምራች ድርጅቶችና መጋዘኖችን በማጥቃት፣ ከእርሻ እስከ ገበያ ባለው ሰንሰለት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር በማድረግ፣ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችና ነዳጆችን ለማስተጓጎል የማስገቢያ ኮሪደሮችን የመቆጣጠር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር እንዲባባስ እንደሚያደርግም በሰነዱ ተገልጿል፡፡

ጦርነት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ሆነ ብሎ ማጥቃት፣ ማቃጠል፣ ማውደም በግልጽ ታይቷል ብለዋል ዶክተር አቡሌ።

የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ማውደም መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ የሚመጡ የውጭ ባለሃብቶችን እንቅስቃሴ በመገደብ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚገኘውን ገቢም ያሳጣል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም