ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ተቀራርባ መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ

68
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ። ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በኢትዮጵያ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የግብጽ አምባሳደር አቡበከር ሄፍኒ ማህሙድ በጽሕፈት ቤታቸው አግኝተው አሸኛኘት አድርገውላቸዋል። አምባሳደር አቡበከር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከር ላደረጉት አስተዋጽኦ ወይዘሮ ሂሩት አመስግነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ያላት ሁለንትናዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠውላቸዋል። አምባሳደር አቡበከር ማህሙድ በበኩላቸው በቆይታቸው ለኢትዮጵያ እና ግብጽ የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ በኢትዮጵያ መንግስት ለተደረገላቸው እገዛ አመስግነዋል። የሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብርም የበለጠ መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያና የግብጽ የህዝብ ለህዝብ እና ኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስም ሁለቱ አገሮች በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም