በቡራዩ አካባቢ ሰላም በመስፈኑ ዲፕሎማቶች ተረጋግተው መንቀሳቀስ ይችላሉ - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

91
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 በአዲስ አበባ ዙሪያ ቡራዩ አካባቢ ሰላም በመስፈኑ ዲፕሎማቶች ተረጋግተው መንቀሳቀስ እንደሚችሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ ለሚኖሩ አምባሳደሮችና የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት በወቅታዊ የአገሪቷ ጸጥታ ዙሪያ ዛሬ በአዲስ አበባ ማብራሪያ ሰጥቷል። ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እንዳሉት፤ ከአዲስ አበባ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ቡራዩ ከተማ አካባቢ ግጭት ተከስቶ ነበር። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች "ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ ሰዎችም ሞተዋል"  ብለዋል። በተጨማሪም ግጭቱን በማውገዝ በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ከወጡት መካከል አምስት ሰዎች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በፈጠሩት ግብግብ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል። በቡራዩ የተከሰተው ግጭት በተደራጁ ቡድኖች ሲመራ እንደነበር ገልጸው፤ መንግስት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። በዚህም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ሰባት መቶ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርምራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም በአዲስ አበባ ያሉ አምባሳደሮችና የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላሙ የተለመሰ በመሆኑ ተረጋግው መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አምባሳደሮችና የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላትም ኢትዮጵያ በመልካም ለውጥ ላይ መሆኗን መስክረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ከግብ እንዲደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም