የዞኑ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው በመጠበቅ የአሸባሪዎችን እኩይ ሴራ እያጋለጡ ነው

127

መቱ መስከረም 9/2015 (ኢዜአ) የኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው በመጠበቅ የአሸባሪዎችን እኩይ ሴራ እያጋለጡ መሆኑን ገለጹ።

ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅና በሴረኞች ፕሮፓጋንዳ እንዳይረበሽ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ገልጿል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች እንዳሉት አንድነታቸውን በማጠናከር አካባቢያቸውን ለጠላት የማይመች እንዲሆን እየሰሩ ነው።

በዞኑ የመቱ ወረዳ ነዋሪዎች ሰላም ሲረጋገጥ ዋና ተጠቃሚዎቹ እኛ እንደሆንን ሁሉ ሰላምን በማረጋገጥ ስራ ውስጥም በግንባር ቀደምትነት እየሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ነዋሪዎቹ በየአደረጃጀቶቻቸው የአከባቢያቸው ሰላም እየጠበቁ የተለየ እንቅስቃሴ ሲያጋጥማቸው ለህግ አካል በማሳወቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወረዳው ነዋሪ አቶ አማረ ክብረት ከዚህ ቀደም አሸባሪው ሸኔ ወደ ወረዳቸው ለመግባት ሞክሮ እንደነበረ አንስተዋል።

ሆኖም የአካባቢው ሕዝብ በአንድነት የአሻባሪው ቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

ሌላው አስትያየት ሰጪ አቶ አዝመራ ቶኮን "ለሰላማችን በግንባር ቀደምትነት ዘብ መቆም ያለብን እኛው መሆናችንን አውቀን እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።

"የሰላም ጉዳይ እንዱ የሚጠብቀውና የሚያረጋግጠው ሌላው ደግሞ ከሚገኘው ሰላም ተጠቃሚ የሚሆንበት ሳይሆን ሁሉም ጠባቂና ተጠቃሚ መሆን አለበት'' ሲሉ ተናግረዋል።

''ሰላምን ለማረጋገጥ ትልቁና ዋናው ጉዳይ አንድነትን ማስጠበቅ ነው'' ያሉት የመቱ ወረዳ የአስተዳደርና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸብር አለባቸው ናቸው።

በወረዳው በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ እንደሚኖሩ ገልጸው ያለምንም ልዩነትና የፀጥታ ስጋት ሰላማቸውን የማረጋገጥና የማስቀጠል ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ተላላኪውን የሸኔ ሽብር ቡድን የመቃወም አመለካከቶቹንም ከኅብረተሰቡ የማጥራት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ሕዝቡም ቡድኑ እንደማይወክለው በተቃወሞ ሰልፎችና በሌሎች መንገዶች እተገለጸ ሆኑን ተናግረዋል።

የኢሉባቦር ዞን አስተዳደሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ የዞኑን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል በፀጥታ አካላትና በኅብረተሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሽባሪው ሕወሓት ተላላኪዎች ሕዝቡን በሴራና በፕሮፓጋንዳ እንዳይረብሹት ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ መፍጠር ስራዎች በመስራትና የኅብረተሰቡን አንድነት የሚያጠናክሩ ስራዎች እንደሚሰሩ አክለዋል።

የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመንግስት ሰራተኞች በቅንጅት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በማስረዳት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም