የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያና ኳታር ግንኙነት ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን የያዘ ነው - አምባሳደር ፈይሰል አልይ

110

መስከረም 9 ቀን 2014(ኢዜአ) የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያና ኳታር ግንኙነት ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን የያዘ ነው ሲሉ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አልይ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኳታሩ ፔንንሴላ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኳታርና ኢትዮጵያ ያላቸው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትንና ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ የተሳሰረ መሆኑን አብራርተዋል።

በባለ ብዙ መስኮች የተሳሰረው ግንኙነቱ በተለይም በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን ያቀፈ ነው ሲሉ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ያለው ሰፊ የኢንቨስትመንት እድልና መስህቦች ለኳታር ባለ ሃብቶችና ቱሪስቶች ልዩ መዳረሻ ይሆኗቸዋል በማለት ነው ያመለከቱት።

የሀገራቱ ትስስር ማሳያ ከሆኑት መካከል በኳታር የልማት ፈንድ አማካኝነት በአዲስ አበባ የሚገነባውን ልዩ የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል በማሳያነት ያነሱት አምባሳደር ፈይሰል የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተፈራረሟቸው 13 ስምመነቶች መኖራቸውንና የተወሰኑት ወደ ትግበራ እንደገቡ ገልጸዋል።

ሀገራቱ ያላቸውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ስራ መግባታቸውንና በኳታር ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ለስራ መሰማራታቸውን አንስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ የተከፈተው የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እያደረገች ካለችው ከፍተኛ እንቅስቃሴ መካከል ዋነኛው መሆኑንም በማብራራት የኳታር ባለሃብቶችን እድሉን በመጠቀም በቴክኖሎጂ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናና ቱሪዝም ዘርፎች እንዲሰማሩ ጠይቀዋል።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ የኢንቨስተመንት መስኮቸን ለውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ክፍት ከማድረግ አካያ መንግስት ከፍተኛ እርመጃዎች መውሰዱንና በቅርቡም በፋይናንስ ሴክተሩ የውጭ ተቋማት እንዲሳተፉ የሚያስችል ረቂቅ መቅረጹን ጠቁመዋል።

በኳታርና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብና መንግስት ለመንግስት ግንኙነት በተጠናከረ ሁኔታ ለማሳኬድ እንደሚሰሩም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም