ከውልደት እስከ ሞት በሽብር እና በውሸት

256

የህወሃት የሽብር ቡድን ‘የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ሰነድ ነሃሴ 8 ቀን 2014 ዓም ሾልኮ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ ባዘጋጀው በዚህ ሰነድ ላይ ከውልደት እስከ ሞት በሽብር እና በውሸት እንደሚዘልቅ በይፋ ያስመሰከረበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ቡድኑ ቅጥፈት በተሞላበት ሰነዱ ላይ የእምዬን ወደ አብዬ አይነት የሚመስሉ ሀሳቦችን አስፍሯል፡፡ በዚህም ትክክለኛ የፋሺስት ተግባር እየፈጸመ ያለው ራሱ ሆኖ ሳለ የፌዴራል መንግስቱን ፋሺስት ሲል ይጠራል፡፡ ለዚህም ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች በሰው፣ በእንስሳት እና በንብረት ላይ በቀጥታ የፈጸመውን እንዲሁም በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች በቀጥታ እና በተልዕኮ የፈጸማቸውን እና ያስፈጸማቸውን ዘግናኝ ጥቃቶች፣ ዘረፋዎች እና ውድመቶች ማንሳት ለፋሽታዊ ተግባሩ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡

ቡድኑ ለህዝብ ጥቅም እንዳልቆመ ግልጽ ሆኖ የታየው ህዝብ ሲያነሳ የነበረውን የለውጥ ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ህዝብን በማፈን በለመደው ለዘረፋ የሚመቸው የስልጣን ማማ ላይ ለመቆየት ያልፈጸመው እና ያላስፈጸመው ወንጀል ምን አለ? ያልሰነዘረው የቱን የሽብር ጥቃትስ መጥቀስ ይቻላል? ቡድኑ በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ትብብር በ2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ በመቃወም ወደ ጎሬው ከመግባቱ በፊትና ከገባ በኋላ ፌዴራሊስት ነኝ በማለት እንደለመደው በብሄር ብሄረሰቦች ስም ለመነገድ ያልቆፈረው ጉድጓድ ያላደራጀው ምስ ለኔም አልነበረም፡፡

ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ሆነና ነገሩ በጊዜ ሂደት የሽብር ቡድኑን ውስጣዊ ሴረኝነት ሲረዱ ሁሉም አንተባበርህም በማለታቸው አንድም ልክ እንደሱ በሽብር ተግባራት ላይ ከተሰማሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አሸባሪ ቡድኖች ጋር ወዳጅነት መስርቶ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ህዝብን ማጥቃት ስራዬ ብሎ ተያያዘው፡፡

ይህ ቡድን ህብረ-ብሄራዊ/ፌዴራሊስት ነኝ ይበል እንጂ በተግባር የነበረው እና አሁንም ድረስ እየተከተለ ያለው የፖለቲካ መስመር ከአንድ እኔ በስተቀር ሌላ አያስፈልግም የሚል የስግብግብ እና የጥቅመኝነት አባዜውን ነው፡፡ ለዚህም አንድም አማራጭ ሃሳብ ያለው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በክልሉ እንዳይንቀሳቀስ ማፈኑን፣ ማሰሩን እና ማገዱን መጥቀስ ይበቃል፡፡ ይሁንና በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን አቅፎ የተመሰረተውን የፌዴራል መንግስት አሃዳዊ በሚል መጥራቱም እንዲሁ ቡድኑን ለትዝት ዳርጎታል፡፡

በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የግሉ መገለጫ የሆነው ይህ የሽብር ቡድን ቀደም ሲል ከአማራ ህዝብ ጋር ቆጥረን ሂሳብ እናወራርዳለን ሲል በቆየበት አንደበቱ እንዲሁም በቅርቡ ሾልኮ በወጣው ሰንዱ የአማራ ተስፋፊ ሃይል በቆየ የትምክህት ታሪኩ፣ ተስፋፊነቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመጫን የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ ከወረራው በላይ፣ የተደራጀ ዘረፋ፣ ግድያና ሴቶችን የመድፈር የመሳሰሉ ወንጀሎችን ፈጽሟል ይላል። እነዚህን ህገ-ወጥ ተግባራት በተናጠልም ሆነ በጅምላ ሲፈጽም የቆየው ራሱ ሆኖ ሳለ ለሌላ መስጠቱ በርካቶችን አስገርሟል፡፡

አሁን የተፈጠረው አጋጣሚ በሌሎች ክልሎች ቢሆን ኖሮ ለትግላችን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነበር። ነገር ግን ይሄ ሁኔታ የተፈጠረው በአማራ ክልል መሆኑ ከዚህ ሀይል ጋር ወዳጅነት ሊኖረን አይችልም፤ ይልቁንም በጠላትነት እንፈርጀዋለን ባለበት አፉ አሁን ላይ ደርሶ ከአማራ ህዝብ፣ ኤሊት፣ ፋኖ፣ ልዩ ሀይል ሆነ ሚሊሻ ምንም ጠብ የለንም ሲል የተለመደ መደለያ ለማቅረብ ሲሞክር ይደመጣል። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ የሚለውን ብሂል የዘነጋ በሚመስል መልኩ ይህን ማለቱ ትዝብት ላይ ጥሎታል፡፡

ቡድኑ ዕኩይ ዓላማውን ለማስፈጸም በዋናነት የሀሰት መረጃ ማሰራጨትን ጨምሮ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ፤ መፈጸም የሚችለውን ሁሉ እንደሚፈጽም፤ መፍጠር የሚገባውን ጥምረት ሁሉ ከማንም ጋር ቢሆን እንደሚፈጥር በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር አሳይቷል። ለዚህም ነው በሰነዱ ላይ በተለይም የልዩነት ነጥቦችን በማህበራዊ ሚዲያ በማጉላት ህዝብ እና መንግስትን ለመነጠል ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስረግጦ መጠቆሙ።

ይህ የሽብር ቡድን ስልጣን ላይ በቆየበትም ሆነ አሁን በለየለት የሽብር ተግባር ላይ በተሰማራበት ወቅት በየደረሰበት መግደል፣ ሴቶችን መድፈር፣ ንብረት መዝረፍና ማውደም ግብሩ መሆኑን በቅርቡ ባወጣው ሰነድ ላይ በፈጸመው፣ ለሚፈጽመው የሽብር ተግባራት፣ ለንብረት ዘረፋ፣ ውድመት እንዲሁም ሀገር ለማፍረስ ሰርጎ ገቦችን በተፈናቃይና በተጓዥ ስም አስቀድሞ እንደሚልክ ነገር ግን ይህ ሰርጎ የሚገባው ሀይል ልክ እንደከዚህ በፊቱ የምዝበራና ዘረፋ ተግባር እንዳይሳተፍ ሲል የማስመሰል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ቀደም ሲል በአፍሪካ ህብረት የሚካሄደው የሰላም አማራጭ ህብረቱም ሆነ ልዩ ልዑኩ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ልዩ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ለእኔ አይጠቅመኝም። በአፍሪካ ህብረት ላይ እምነት የለኝም። የግድ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ተወካዮች ካላደራደሩ ሲል ቆይቶ በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት በሚደረገው የሰላም አማራጭ ላይ ለመሳተፍ ተስማምቻለሁ ማለቱ እንደለመደው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር ያስችለኛል ከሚል የተለመደ የክህደት ተፈጥሮአዊ ባህሪው የመነጨ መሆኑን ቡድኑ ያለፈባቸውን ጊዜያት በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ በርካቶች እየተናገሩት ይገኛሉ፡፡  

ቡድኑ ክህደት እና ውሸት ጥርሱን ሲነቅል ያደገበት ሁነኛ መገለጫ ባህሪው መሆኑን ራሱ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ በግልጽ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለህ አስመስለህ እራስህን ማቅረብ መሆኑ ሊረሳ አይገባም በማለት በግልጽ አስቀምጦታል። ከዚህ መነሻነትም ቡድኑ መሰል ተግባራትን በስልጣን ላይ እያለም ጭምር ባዘጋጃቸው ተከፋይ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሀሰተኛ የፈጠራ መረጃዎችን በማሰራጭት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሲያታልል መቆየቱን የሚናገሩም በርካቶች ናቸው፡፡

ቡድኑ ከጦርነት አባዜ ውጪ በሰላም ላይ የተመሰረተ ምንም አይነት ሰላማዊ ተሞክሮም፣ ልምድም ሆነ ፍላጎት እንዳልነበረው፣ እንደሌለውና ወደፊትም እንደማይኖረው የሚያመላክቱ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለዚህም በቅርቡ የፌዴራል መንግስት ህዘቡ ሰላም እንዲያገኝ በሚል የወሰዳቸውን ፖለቲካዊ የሰላም አማራጮች በሙሉ በመግፋት ህዝቡ ከጦርነት አዙሪት እንዳይወጣ ያደረገበትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቡድኑ ለሰላም ያለውን አላርጂክነት ህዝቡም በጦርነት አዙሪት ውስጥ ተዘፍቆ እንዲቆይ ለማድረግ የቀረበውን የሰላም አማራጭ እንደማንቀበል ደጋግመን ለሕዝባችን ገልፀናልየሕዝባችን ዘላቂ የሰላም ዋስትና የሚረጋገጠው በክንዳችን ብቻ መሆኑን በፅኑ እናምናለን በማለት የገለጸው፡፡ የሽብር ቡድኑ የያዘውን የግል እና የቡድን ፍላጎት ለማሳካት ምንም አይነት መጠን ያለው ህዝብ ቢያልቅ ደንታው እንዳልሆነ በሰነዱ ላይ የተጠየቀውን ያክል የሕይወት መስዋእትነት ህዝቡ እንዲከፍል እንደሚያደርግ አስፍሯል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን ሀገር ለማፍረስ በሚከተለው አፍራሽ አካሄድና በንጹሃን ላይ በሚያደርሰው የሽብር ጥቃት ብቻውን እንዳልሆነና ሌሎች በህዝብ ደም ርካሽ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከተጠመዱ የውስጥና የውጭ ግብረ-አበሮቹ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ለዚህ ደግሞ የራሳችንና የአጋሮቻችን ዝግጁነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የውስጥ ትግላችን በማገዝ የሚንቀሳቀሱ እንደ ኦነግ የመሳሰሉ አጋሮቻችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ አጋዦቻችን በዚህ ጊዜ የተሳካ ጥምረት በማድረግ  በምናደርገው እንቅስቃሴ ከጎናችን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን የክልላችን ዋና ስራ አስፈፃሚ በዝግ ባደረገው ውይይት አረጋግጧል ይላል።

ይህ ቡድን ዕኩይ ዓላማውን ለማሳካት ወጣቶችን በተሳሳተ መረጃ ወደ ጦርነት መማገድን እንደስልት እንደሚጠቀም የትግራይ ወጣቶችን አሁን የሚደረገው ትግል ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ የመጨረሻ ምዕራፍ ትግል እንደሆነ፤ ድል አይቀሬ መሆኑን መላው የትግራይ ክልል ወጣትና ሕዝቡን ማሳመን እንደሚገባ ገልጿል። በዚህም ቡድኑ ወላጆችን ያለ ጧሪ ቀባሪ ማስቀረቱን በተግባር አሳይቷል።

አብዛኞቹ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶችም የሽብር ቡድኑ ተባባሪ መሆናቸውን ቡድኑ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ በትግራይ የሚገኙ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ለምናደርገው ትግል ደጋፊ እንዲሆኑና ከጎናችን እንዲቆሙ፤ ሰብአዊ ድጋፍ ማከማቻ መጋዘኖች በምናደርገው ትግል ወታደራዊ ስንቅ አቅርቦት እንዳይጓደል በቁጥጥራችን ስር ልናደርጋቸው ይገባል ሲል ጠቁሟል። በቅርቡ በሽብር ቡድኑ ነዳጅ ተዘረፈብኝ ያለው የዓለም ምግብ ድርጅት ተዘረፍኩ ከማለት ባለፈ በቡድኑ ላይ የወሰደው አንዳችም ርመጃ አለመኖሩን ላስተዋለ ትብብሩ መኖሩን ያረጋግጣል።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ከደረሰበት ወታደራዊ ኪሳራ እንዲያንሰራራ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት እንደሚደግፉት ሲገልጽም፤ በውጭ ያሉ አጋዦቻችን በአስቸጋሪ እና አጣብቂኝ ጊዜ ውስጥም ቢሆን ችግሩን አልፈው ዘመናዊ ትጥቆች እንድንታጠቅ አድርገውናል ይላል ይህ በስውርም ሆነ በግልጽ የተመሰረተ ግንኙነት ቀጣይነት እንደሚኖረው እና የጋራ ግባቸው በውጤታማነት እስኪጠናቀቅ ድረስም እንደሚቀጥል፤ የዚህ ዘመቻ ምዕራፍ መራርና በርካታ መስዋእትነት የሚጠይቅ በመሆኑ አሁንም ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ዘመናዊ ትጥቅ ለመከላከያ ሃይላችን እንዲያቀርቡልን የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከውስጥና ከውጪ ተባባሪዎቻችን ጋር ያለንን ስራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ይላል።

በመደበኛ ወታደራዊ አቅም ከፌዴራል መንግስቱ ጋር እንደማይመጣጠን ቀድሞ የተረዳው የህወሃት የሽብር ቡድን ሽብር፣ ፍርሃትና የስነ ልቦና ጫና መፍጠርን እንደስልት እንደሚጠቀም ለዚህም ተከፋይ የሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጪ መገናኛ ብዙሃንን እንደሚጠቀም ባለቤቶቻቸው አዲስ አበባ የሚገኙ ሚዲያዎችና ዩቲዩብ ቻናሎች ከፍተኛ ድጋፍ ስለሚኖራቸው የመረጃና ፋይናንስ ድጋፋችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል በግልጽ አስቀምጧል። 

ለስልጣኑ መረጋገጥ ከሆነ ልማትን ማውደምም ሆነ ማደናቀፍ እንዲሁም ህዝብ መጎሳቆል ለቡድኑ ምኑም እንዳልሆነ መንግሥት በችግር ጊዜ አሳክቼዋለሁ የሚላቸውን የእርሻ ዘርፍም ሆነ የኢኮኖሚ ልእልና በማደናቀፍ ወደ ኋላ መመለስ፤ ሕዝብ በማንቀሳቀስ የጀመረው የእርሻ ልማት፣ ስንዴና ሌሎች የኢኮኖሚ ስራዎች ማደናቀፍ ላይ ትኩረት እናደርጋለን ይላል። ለዚህም የእርሻ ዘርፉ እንዲደናቀፍ በየአካባቢው ግጭት በመቀስቀስ እና ግጭት ለመቀስቀስ የሚያስችሉንን ሃይሎች በማገዝ እረፍት መንሳትን እንደስልት እንጠቀማለን ብሏል።

ቡድኑ አሳካዋለሁ ላለው ዕኩይ ፖለቲካዊ ሴራዎች በማስፈጸሚያነት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል ዋናው፤ በመንግሥት ላይ ሕዝብ እንዲያምፅና ፈጣን የስርአት ለውጥ እውን እንዲሆን ኢኮኖሚውን ማቃወስ ለነገ የማይባል ስራ ነው፤ የሚል ግልጽ የውንብድና ተግባርን ጠቅሷል። ለዚህም የተመረጡ አምራች ድርጅቶችንና መጋዝናቸውን ማጥቃትና ማፍረስ፣ ከእርሻ እስከ ገበያ ባለው ሂደት የዕለት አስቤዛ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖረው ማድረግ፣ ከውጪ የሚገቡ ሸቀጦች እና ነዳጅ እንዲስተጓጎል ማድረግ፣ ዋና ዋና የማስገቢያ ኮሪደሮች በመቆጣጠርና ሌሎች እርምጃዎችን በመውሰድ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ችግር እንዲፈጠር እና እንዲባባስ ማድረግ ዋናው ትኩረታችን እናደርገዋልን ይላል። መሰል የውንብድና ተግባር ከአንድ ከራሱ በላይ ለህዝብ ማሰብ ከማይችል አሸባሪ ቡድን የሚጠበቅ መሆኑን ሁሉም ከተረዳው ውሎ አድሯል። በመሆኑም መላ ህዝቡ መንግስት የሚሰራውን የመከላከል ስራ የማገዝ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የቡድኑን ዕኩይ ተግባር ማውገዝ፣ ማጋለጥና መመከት ይጠበቅበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም