ባንኩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎቱን ለማስፋፋት ያስገነባውን የዳታ ሴንተር አስመረቀ

141

ባህርዳር፤ መስከረም 7/2015 (ኢዜአ) ፀደይ ባንክ አክሲዮን ማህበር ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ አገልግሎቱን ለማስፋፋት በ370 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን የዳታ ሴንተር ዛሬ አስመረቀ።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የዳታ ሴንተሩ ምርቃት የተካሄደው።  

ፀደይ ባንክ አክሲዮን ማህበር በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ካፒታል ከ11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተመልክቷል። 

በምርቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምወሰን ፤ ወደስራ ከመግባታቸው በፊት ለባንኩ የፋይናንስ ስራ መቀላጠፍ የሚያግዝ ቴክኖሎጂን ቅድሚያ ተሰጥቶ መገንባቱን ገልጸዋል። 

የዳታ ሴንተሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን የሚያሳድግና በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚገኙ ቴክኖሎጂዎችን ያሟላ መሆኑን ተናግረዋል። 

ባንኩ ስራውን ሲጀምር የሚያጋጥመውን ክፍተት ቀድሞ በመድፈን ጥራት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት ለደንበኞች መስጠት ያስችለዋል ብለዋል።

ከአንድ ሳምንት በኋላም ባንኩ በይፋ ተመርቆ ስራውን በመጀመር በመላ ሀገሪቱ ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት ጠቅሰው በአፍሪካ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም ዋና ስራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል።

የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ፀደይ ባንክ በክልሉ ድህነትን ለመቀነስና በኢዮጵያ የፋይናንስ ገበያ ትልቅ አቅም ይዞ መንቀሳቀስ የጀመረ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተበዳሪ ደንበኞች ያሉት ባንኩ በተለይ ለአርሶ አደሩ ብድርና ግብዓት ከማቅረብ በተጨማሪ ከሴቶችና ወጣቶች ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳለው ገልጸው ከ12 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት አመልክተዋል። 

በቀጣይ በመላ ሀገሪቱ ተደራኝ ለመሆንና በአፍሪካም ተወዳዳሪ ከሆኑ ባንኮች አንዱ ለመሆን ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዳታ ሴንተር መገንባቱን ነው የገለጹት።

ባንኩ ስራ ከመጀመሩ በፊት የገነባው የዳታ ሴንተ ማዕከል ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ ያስችለዋል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው ።

ለልማቱ መፋጠን የፋይናንስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ "የቀድሞው አብቁተ የአሁኑ የፀደይ ባንክ አክሲዮን ማህበር በተደራሽነቱና በአገልግሎት ሰጪነቱ ተኪ የሌለው ተቋም ነው" ብለዋል። 

ባንኩ ለአርሶ አደሩና ለዝቅተኛ ነዋሪው ህዝብ የብድር አገልግሎት በማቅረብ ሲሰራ የቆየ እንደሆነ ተናግረዋል። 

ተቋም በቀጣይ ወደባንክ ሲሸጋገር ከ80 በመቶ በላይ ለሆነው የክልሉ አርሶ አደር ህይወት መቀየርና የህዝቡን የፋይናንስ ችግር በማቃለል ከድህነት እንዲላቀቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስትም ከባንኩ ጋር አብሮ በመስራት የአርሶ አደሩ ልማት እንዲሳካና ኑሮው እንዲሻሻል ለሚያደርገው ስራ ሁሉ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሁኑን አስታውቀዋል።

የቀድሞ /አብቁተ/ የአሁኑ ፀደይ ባንክ አክሲዮን ማህበር በ1988 ዓ.ም በ3 ሚሊዮን ብር ካፒታል 40 ሰራተኞችን ይዞ ስራውን በ6 ወረዳዎች እንደጀመረና አሁን ላይ ጠቅላላ ካፒታል ከ11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተመልክቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም