ኢትዮጵያን በባንዳና የጥፋት ተላላኪዎች ለማፍረስ የሚደረገውን ጥረት ህዝብና መንግስት በጋራ ሊመክቱ ይገባል- የህግ ባለሙያ

84

መስከረም 7/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በባንዳና የጥፋት ተላላኪዎች ለማፍረስ የሚደረገውን ጥረት ህዝብና መንግስት በጋራ ሊመክቱት እንደሚገባ የህግ ባለሙያው ኪያ ጸጋዬ ተናገሩ።

የኢትዮጵያን ጠላቶች ሴራ ለማክሸፍ በሚደረግ ትግል ውስጥ ሁሉም የድርሻውን ለማበርከት መዘጋጀት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በእነርሱ ፈቃድ ያልሆነ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይጀመር ቢጀመር እንኳን እንዲደናቀፍ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የህግ ባለሙያው ኪያ ጸጋዬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ጠላቶቿ አንዳንዴ ጦር ሰብቀው ሌላ ጊዜ ደግሞ የውስጥ ባንዳዎችን ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ ነው። 

የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ ከቀደሙ አያቶች የተረከበው የአሁኑ ትውልድ የራሱን ታሪክ ሰርቶ ማለፍ አለበት ሲሉ ነው የገለጹትው።

የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደ አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ያሉ የጥፋት ቡድኖችን በማስተባበር አገር ለማፍረስ የሚፈጽሙትን የጥፋት ተግባር መንግስትና ህዝብ በጋራ መመከት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በቅርቡ በተካሄደው የአዲስ ወግ ውይይት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እርስ በርስ እንድንባላ በማድረግ ጥቅማቸውን ለማሳካት ረጅም እርቀት እየተጓዙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በቀጥታ መዋጋት የማይችሉና የማይፈልጉ ሃይሎች የውስጥ ተላላኪዎቻቸውን በመጠቀም ሰላም የመንሳት ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ክብርና ልዕልና ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ በመክፈል ኢትዮጵያን በጽኑ መሰረት ላይ ማኖር አለብን ነው ያሉት።

ከአሸባሪው ህወሃት በቅርቡ ሾልኮ የወጣው "የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ" በሚል የተዘጋጀው ሰነድም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ምን ያክል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክቷል።

የህዝብን አብሮነት መበጣጠስ፣ ልማቱን ማደናቀፍ፣ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ጭምር በመስራት አገርን እረፍት መንሳት ከሰነዱ ቁል ጉዳዮች መካከል መሆኑ ተረጋግጧል።

ለአሸባሪው ቡድን የጦር መሳሪያ ለማድረስ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ ለመግባት ሲሞክር በቅርቡ በኢትዮጵያ አየር ሀይል ተመትቶ የወደቀው አንቶኖቭ አሸባሪው ህወሃት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ  ጠላቶች ጋር በማበር አገር ለማፍረስ የሚያደርገውን ጥረት ያሳየ መሆኑም ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ከቁስ እስከ ታሪክና ቅርስ በመስረቅ አገርንና ህዝብን ታሪክና ማንነት አልባ ለማድረግ የሚሰራ አሸባሪ ቡድን መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

አሸባሪው ህወሃት ህፃናትን ጨምሮ ህዝብን በገፍ ወደ ጦርነት በማስገባት በተለያዩ አካባቢዎች 3ኛ ዙር የጦር አውደ ግንባር መክፈቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም