የቤንዚን እጥረት ለትራንስፖርት ችግር እንዳጋለጣቸው የነገሌ ከተማ አሽከርካሪዎችና ነዋሪዎች ገለጹ

68
ነገሌ መስከረም 9/2011 በነገሌ ከተማ የቤንዚን እጥረትን በማባባስ አንዱን ሊትር በ40 ብር ሂሳብ የሚሸጡ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አሽከርካሪዎች ገለፁ ። የነገሌ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ የቤንዚን እጥረቱን ለማቃለል ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር አፋጣኝ መልስ እንደሚሰጥ አመልክቷል። በከተማው የ03 ቀበሌ ነዋሪና የባጃጅ አሽከርካሪ አቶ በርገና በርዛ በሰጡት አስተያየት በከተማው የቤንዚን እጥረት በመከሰቱ ጥራት የሌለው አንድ ሊትር ቤንዚን ከግለሰብ በ40 ብር ሒሳብ በመግዛት ለመስራት መገደዱን ተናግሯል ። አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን እያላቸው ደብቀው ለቸርቻሪዎች  አሳልፈው በመስጠት በትርፍ እየሸጡ መሆናቸውን ቢጠቁሙም እስካሁን የተወሰደ ርምጃ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ “በህጋዊ መንገድ በ19 ብር ከ25 ሳንቲም መሸጥ የነበረበትን አንድ ሊትር ከግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ በ40 ብር ሒሳብ እየተሸጠ በመሆኑ በነዳጅ ማደያዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል” ብለዋል፡፡ ሌላው የባጃጅ አሽከርካሪ ወጣት ለማ ሰቦሳ እንደገለፀው በችርቻሮ የሚሸጠው ቤንዚን ከናፍታ ጋር የተቀላቀለ በመሆኑ ከዋጋውም በላይ በተሽከርካሪዎች ላይ ችግር እየፈጠረ ነው። በማደያዎች አቅርቦት ችግር ለሁለት ሳምንት በተፈጠረ የቤንዚን እጥረት አንድ ሊትር በ40 ብር ገዝቶ ቀደም ሲል በወጣው ታሪፍ ለመስራት ሞክሮ ለኪሳራ መዳረጉንም ገልጿል፡፡ ለህዝቡ ተገቢውን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የቤንዚን አቅርቦቱ ችግር እንዲፈታ ወይም በጊዜያዊነት ታሪፉ እንዲስተካከልም ጠይቋል። የከተማው ነዋሪና የባጃጅ ተጠቃሚ ወይዘሮ እየሩስ በዳኔ ቤንዚን ጠፍቷል በሚል ሰበብ አንዳንድ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ለሁለት ብር መንገድ አምስት ብር እያስከፈሉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የነገሌ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የንግድ ስራ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ኢያ መሊቻ በአቅርቦት እጥረት ለሶስት ሳምንት በማደያዎች ቤንዚን እንዳልነበረ ገልጸዋል፡፡ “በተወሰኑ ማደያዎች የነበረ ሰባት ሺህ ሊትር ቤንዚን አሽከርካሪዎች በፍትሀዊነት እንዲጠቀሙ ኩፖን ከመስጠት ጀምሮ ክትትልና ቁጥጥር ሲደረግ ቆይቷል” ብለዋል፡፡ ከዛሬ ከመስከረም 9/2011 ጀምሮ የተባበሩትና ኖክ በሚባሉ ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ቤንዚን እየወረደ በመሆኑ ችግሩ በመጠኑ እንደሚቃለል ጠቁመዋል፡፡ “በከተማው ውስጥ በባለሙያዎች ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ በመሆኑ በህገ-ወጥ ድርጊት የተሰማሩት ተጠያቂ ይሆናሉ” ብለዋል፡፡ የኦይል ሊቢያ ነዳጅ ማደያ ባለቤት አቶ ወንዶሰን ዘውዴ “እጥረቱ የተፈጠረው በአቅርቦት ችግር እንጂ ቤንዚን ካለ ለአንዱ ሲሸጥ ለሌላው የሚከለከልበት ምክንያት የለም” ብለዋል፡፡                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም